የዶክተር መረራ ጉዲና መፈታት ለኢትዮጵያ ሰላምና ፍትህ በጎ አስተዋጽኦ ያደርጋል

የዶክተር መረራ ጉዲና መፈታት ለኢትዮጵያ ሰላምና ፍትህ በጎ አስተዋጽኦ ያደርጋል
የፊታችን ረቡዕ January 17 ይፈታሉ።
 
አንዳንዶች እንደምታስታውሱት ዶክተር መረራ የታሰሩ ጊዜ መግለጫ አውጥተን ነበር። እርሳቸው በሳል የፖለቲካ መሪ እንደሆኑና ለሚደረጉ የሰላምና የመግባባት ጥረቶች ሁሉ ተባባሪ እንደነበሩ። ሆኖም ግን መንግስት በወንጀል ጠርጥሮ እንዳሰራቸውም ጠቅሰን ነበር።
በአገልግሎታችን ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ መንግስትንና ተቃዋሚዎችን ፊት ለፊት የማቀራረብና የማነጋገር ስራ እንሰራለን። በዚህ ሂደት ውስጥ አንዱ ቁልፍ ተሳታፊ ዶክተር መረራ ነበሩ።ለሰላምና ፍትህ መስፈን ያላቸውን ፍላጎትና ትጋት አደንቃለሁ። በኋላ ግን ከመንግስት ባለስልጣኖች ሁከትን በማነሳሳት ወንጀል እንደሚጠረጠሩና ለዚያም ማስረጃ እንዳለ ተነገረኝ። እኔም በወቅቱ ዶክተር መረራ በወንጀል ስራ ይሳተፋሉ ብዬ እንደማላምንና እኔ እስከማውቃቸው ሰላማዊ እንደሆኑ ተከራከርኩ። ቢሆንም ግን ይሄንኑ መረጃ ወዲያውኑ ለዶክተር መረራ በመንገር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳሰብኳቸው።የተፈራው አልቀረም ታሰሩ። በኋላም ጉዳዩን ስንከታተል ቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳና ጉዳዩ ሊታይ ይችላል የሚል ተስፋ አገኘን። አሁን ስለሚፈቱ በጣም ደስ ብሎናል።ለኢትዮጵያ ሰላምና ፍትህ ቁልፍ ሚና አንደሚጫወቱ አውቃለሁ።
እኔ እንደገባኝ ኣሁን ይፈታሉ የተባሉት በክስ ላይ የነበሩ ሲሆኑ ተፈርዶባቸው ያሉት የምህረት ፕሮሰሱ እንዳለቀ ይፈታሉ ብለን እንጠብቃለን።
ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች፥ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች ይፈቱ ዘንድ ጥሪያችን እያቀረብን መንግስት በውጭም ሆነ በውስጥ ካሉ መሳሪያ ካነገቡት ጭምር ጋር በመነጋገር ወደ ሃገራቸው ገብተው በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲሳተፉ እንዲፈቅድ ጥሪ እናቀርባለን።ከዚህ በተጨማሪ የጸረ ሽብር ህጉ ለዲሞክራሲ አሉታዊ ሚና እየተጫወተ ስለሆነ እንዲሰረዝ ወይም እንዲሻሻል እንጠይቃለን።
አገልግሎታችንም ከሌሎች ወገኖች ጋር በመተባበር የብሔራዊ መግባባት ጥረታችንን እንቀጥላለን።
Advertisements

እውነትን ወይስ ፍቅርን…የትኛውን?

እውነትን ወይስ ፍቅርን…የትኛውን?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶሻል ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ የሚታይ ሚዛን ያለመጠበቅ ነገር አለ።ወደ አንድ ጫፍ መስፈንጠር ይበዛል። አንድ ትክክለኛ ነገር ያዝን ማለት በሁሉም ትክክል ነን ወይም ሚዛን የጠበቀ አካሄድ ነው ማለት አይደለም።
በፌስቡክ የሚታየውን ፈር የለቀቀ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት “ፌስዳቢዎች” እንደተባሉ ሰምቻለሁ። የፌስቡክ ተሳዳቢዎች ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሚታየው በሁሉም ጎራ ነው። በተለያዩ ሃይማኖቶችና ቤተ እምነቶች እንዲሁም በፖለቲካው መድረክ አካባቢ ጭምር።ልዩነቱ እስከማይታወቅ ድረስ በእግዚአብሔር ስም የሚሰዳደቡት ከፖለቲካው ያልተለየ ሆኗል። ይህ ምን ማለት ይሆን? በአንድ አጀንዳ ላይ አሸናፊና ትክክል ሆኖ ለመውጣት እግዚአብሔርን ማሰደብና ጥላቻን በመዝራት ከወንድምና እህታችን ጋር ያለውን የፍቅርና የመከባበር መስመር መቁረጥ ምን ይባላል? የወንጌል ዓላማ ሰውን ማዳን ነው ወይስ በኔ መንገድ ካልሄድክ ገፍቼ እጥልሃለሁ ነው?
ጳውሎስ “ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” ሲል እኮ ከመሸናነፍ መንፈስ አልፈን ፉክክር ወደሌለበት ከፍ ያለ አድማስና ልምምድ ውስጥ ነን ማለቱ እኮ ነው።
ለሀገርስ ቢሆን ከራስህ ዜጋ ጋር መጠላላት ምን ይፈይዳል? ነገ እኮ ልትዋለድ ትችላለህ፤ወደኋላ ብትቋጠርም ይሄኔ ዘመድ ትሆናለህ።ወዳንተ ሃሳብ ሰው እንዲመጣ ከፈለክ በምን ሂሳብ ነው ስድብ የሚያመጣው? ወይስ በተስፋ መቁረጥ አጥፍቶ መጥፋት መሆኑ ነው?
መጽሃፍ ቅዱስ በኤፌ4:15 “እውነትን በፍቅር እየያዝን” ይላል። በአንዳንድ ትርጉሞች “እውነትን በፍቅር በመናገር” ይላል።
አንዳንድ ወገኖች እውነትን ስለያዝኩ መቆጣት፤ማውገዝ፤መዝለፍ መብቴ ነው ይላሉ።
ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው እኔ ምን አገባኝ፤ከሰው ጋር በፍቅር አርፌ ለምን አልኖርም፥ምን አጋጨኝ? ይላሉ፤ስህተትን እያዩ ዝም ይላሉ።
እንግዲህ እዚህ ጋር የምናየው ሁለት በተለያየ ጎራ ያሉ ወገኖችን ነው።ሁለቱም ጋር የተወሰነ ትክክል የሆነ ነገር አለ፤ሁለቱም ግን ለጥጠውት መጠኑን አልፈዋል። እንግዲህ እዚህ ጋር ነው “እውነትን በፍቅር” የሚለው የሚገባው፤ሚዛናዊነት የሚገባው እዚህ ጋር ነው ማለት ነው።
እውነት ወሳኝ ነገር ነው። ነጻ የሚያወጣው እውነት ነው፤መፍትሔ የሚሆነው እውነት ነው።
እዚህ ጋር ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፤እውነት ያለው ማን ጋር ነው? የትኛው ጎራ ነው እውነቱ ያለው? በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ከታሪክም ሆነ ከገሃዱ ዓለም የምናየው እውነትን ይዘናል የሚሉ አብዛኞዎቹ እንዳልያዙት ነው።አይ እኔ የተለየሁ ነኝ እኔ ጋር ያለው በእርግጥም እውነት ነው፤ማስረጃውም ይሄ ይሄ ነው እንላለን።አንዳንዴ ያ ነገር ትክክል ቢሆንም ብዙ ጊዜ ሙሉ እውነት ላይሆን ይችላል። ግማሽ ብርጭቆ ውሃ ያዩ ሁለት ሰዎች ተቃራኒ የሚመስል ግን እውነት የሆነ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ። አንዱ ብርጭቆው እኮ ግማሽ ባዶ ነው ብሎ እዚያ ላይ ሲያከር ሌላው ደግሞ ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ እኮ ነው ብሎ ሊጮህ ይችላል።
ሁለት ዓይነ ስውራን ዝሆንን ሲያዩ አንዱ እግሩ አካባቢ በመዳሰስ የዝሆኑ አካል ያ ብቻ ሊመስለው ይችላል፤ሌላው ደግሞ ሌላኛውን አካሉን በመዳሰስ ዝሆን ማለት እርሱ የዳሰሰው ብቻ ሊመስለው ይችላል።
“ከዕውቀት ከፍለን እናውቃለን” ይላል ጳውሎስ።ስለዚህ እውነትን አውቄ ጨርሻለሁ ከማለት ይልቅ የደረስኩበት ይሄ ነው በማለት በትህትና ማስረዳትና የሌላውን ሃሳብ ማክበር አስፈላጊ ነው።ጥልቅ በሆነው በመንፈሳዊና በዶክትሪን ጉዳይ እንኳ ብዙ የምናከብራቸው አብያተ ክርስቲያናትና መሪዎች አይስማሙም። በጥቅሱ ላይ ሳይሆን በትርጉሙ ስለሚለያዩ የየራሳቸው እውነት የሚሉት ትርጓሜ አላቸው። በመሆኑም ትሁት መሆንና ምናልባት እኛ ከምናውቀው ሌላ ተጨማሪ ዕውቀት ካገኘን ተወያይቶ፥ጥያቄ ጠይቆ አቋምን ለመቀየር እንኳ ዝግጁ መሆን አለብን።
“የትም ብትወስደኝ እውነትን እከተላለሁ”፤ በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበት ይሆናል።
ስለዚህ ከምናውቀው የማናውቀው ስለሚበልጥ ለጠብና ለጥላቻ ራሳችንን አናጋልጥ።የደረስንበትን ግን ያለፍርሃትና ማመቻመች እናስረዳ።
ሌላው ፍቅር የሚለው ቃል ነው።ዋው፥ከዚህ የበለጠ ቃል በዓለም ላይ አለ? ተነግሮም ተጽፎም የማያልቅ ከውቅያኖስ የበለጠ ጥልቅ የሆነ የዓለማችን ታላቁ ስጦታ።
ወንጌል “ከሁሉ የሚበልጠው ፍቅር ነው” ይላል።አንድ የብሉይ ኪዳን ሊቅ እንዲህ አለ “የመጽሃፍ ቅዱስ ዋናው መልዕክት አምላክህንና ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ ነው።ሌላው ሁሉ የዚህ ትዕዛዝ ማብራሪያ ነው”። ኢየሱስም “ከትዕዛዛቱ ሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፥ህግም ነቢያቱም በዚህ ተሰቅለዋል” ብሏል። የወንጌል ማዕከላዊ ጥቅስ የሚባለው “ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የሚለው ቃል ነው።
ሰዎች ተዋደው ተጋብተው የሰውን ዘር እንዲተኩ አምላክ ያዘጋጀው መንገድ፥የመኖራችን ምክንያት። የእናት ፍቅር፥የልጅ ፍቅር፥ የወዳጅ ፍቅር፥ የሀገር ፍቅር ወዘተ ባጠቃላይ የህይወታችን ትርጉም ፍቅር ነው።የቃሉን ፊደላት ስንከፋፍል ፍጽምና፥ቅድስና፥ርህራሄ ብዬዋለሁ። ለፍቅር የሚከፈል ዋጋ አይቆጭም። ከመጽሃፍ ቅዱስ ተወዳጅ ምዕራፎች አንዱ 1ኛ ቆሮንቶስ13 ነው።የፍቅር ምዕራፍ ይባላል። እውነትን ያለፍቅር ብንናገር ማን ይሰማናል? መሬት እንኳ ተቆፍራ ካለሰለሰች ፍሬ አትሰጥም።ሴት ልጅን በፍቅር ካልቀረብን የጥቅስ ጋጋታ ብቻ ለትዳርና ለግንኙነት አይማርካትም።
ኢየሱስ “እግዚአብሔር የሚመለከው በእውነትና በመንፈስ ነው” አለ።ምን ማለት ነው? እውነት አይበቃም፥መንፈስ ያስፈልጋል፥ያም ማለት እውነትን የሚያለሰልስ፥በቀላሉ እንዲፈስ፥ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ለሰዎች እንዲበራ የሚያደርግ መንፈሱ ነው። ፍቅር ደግሞ አንዱ የመንፈስ ባህርይ ነው። ስለዚህ እውነት ብቻ ይዞ መሄድ ባልተቆፈረና ባለሰለሰ መሬት ላይ እንደመዝራት፥ሴትን በንግግር ብቻ ለማሳመንና ለማግባት እንደመሞከር ማለት ነው።አይቻልም፥አይሆንም፥ፍሬ አያፈራም፥እውነትን በፍቅር!
በፌስ ቡክ ያለው ደረቅ ክርክርና ጥላቻ ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገር መፍትሔ አያመጣም።

ፌስዳቢዎች አስተውሉ።እድሜያችሁን በከንቱ አትጨርሱት። ለተቺና ለተሳዳቢ የተጻፈ ታሪክም ሆነ የቆመ ሀውልት የለም።ትረሳላችሁ።መረሳት ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻችሁ የሚተርፍ መጥፎ ሌጋሲ፤አሻራ ትታችሁ ትሄዳላችሁ። የተነጋርነው ሁሉ በአምላክ ፊት የሚያስጠይቀን ሲሆን በዘመናዊ ቴክኖሎጂም ቢሆን ሬከርድ ስለተደረገ ብትጸጸቱ እንኳ ለዘላለም ታሪክ ሆኖ ስማችሁን ያጎድፋል።
ባልና ሚስት እውነት እውነት ብቻ ቢሉ አንድ ቀን አብረው መኖር አይችሉም።ለሰላምና ለፍቅር ሲሉ እየተሸናነፉ ነው።
ቤት በግ የሆነ ሰው ፌስ ቡክ ላይ አንበሳ ሲሆን ደስ አይልም።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው እውነትን በፍቅር ተናገሩ። እውነት መሆኑን አረጋግጡ፥ለመማማር ቦታ ይኑራችሁ።
ስለ ፍትህና ሰላም ተናገሩ፥እውነት ነውና፤ስለ ወንጌል ተናገሩ፥ እውነት ነውና። ሁሉ ግን በፍቅር ይሁን።
አንድ የጥንት መነኩሴ ባለው ልዝጋ፥
“በመሰረታዊ ነገሮች አንድነት፥
መሰረታዊ ባልሆኑ ልዩነት፥
በሁሉም ግን ቸርነት።

Reverend Daniel Tassew

መንግስትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰብአዊ መብት ዙሪያ ሊነጋገሩ ነው።

መንግስትና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሰብአዊ መብት ዙሪያ ሊነጋገሩ ነው።

በብዙ መቶዎች ከሞቱ፥በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከታሰሩ በኋላ የተጠራው ይህ ስብሰባ ከማክሰኞ Nov. 29, 2016 ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የሚቆየውም ለ ፫ ቀናት ነው።

ባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ዙሪያ እውነተኛ ውይይት ተካሂዶ ተጨባጭ ለውጥ ይመጣ ዘንድ ጸሎታችን ነው።

ሊመጣ ያለው የአሜሪካ አስተዳደር ከጽድቅ፥ከፍትህና ከዓለም ሰላም አንፃር፤

ግብረሰዶማዊነት፥ፀረ እስራኤልነትና የነጭ ዘረኝነት በነጩ ቤተ መንግስት፤

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአሜሪካ አመራርና ምርጫ ላይ አተኩረናል። ይሄም የሆነው በሁለት ምክንያት ነው፤በአሜሪካ ስለምንኖርና እንደ ጌይ፥ውርጃ፥ስደተኞች፥የድሆች እርዳታ፥የዓለም ሰላም ያሉ ጉዳዮች የወንጌል አጀንዳ ስለሆኑ፥ጸሎታችን በዕውቀት እንዲሆንና ማድረግ የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ ነው። የምንሰጠው መረጃም ሆነ የምናስተላልፈው መልዕክት አንዱን ወገን ለመደገፍ ሳይሆን ዓላማው እውነትን በፍቅር መግለጽ ነው።ያ ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ አንደኛውን ተመራጭ ወይንም ያኛውን ሊነካ ይችላል፤የኛ ዓላማ ግን ያ አይደለም።
ሌላው ምክንያታችን በአሜሪካ የሚሆነው ነገር በኢትዮጵያም ሆነ በመላው ዓለም ላይ ተጽዕኖ ስላለው ነው።
የጥንት ነቢያት በፍትህ፥በድሆችና ስደተኞች፥በክፋት ጉዳይ ቤታቸው እየጸለዩ አልተቀመጡም፤ወደ አደባባይ በመውጣት ሲጮሁና ዕውነትን ሲያውጁ፥ለህዝቡ እውቀትና መልዕክት ሲያስተላልፉ ነበር።
የዘንድሮ ክርስትና የቲዎሎጂ ክርክር፥የእርስ በርስ መፎካከርና መበላላት ነው ። የእኔነት ክርስትና፤ እኔ ልዳን፥እኔ ልባረክ፥እኔ ልበልጽግ፥እኔ ልፈወስ፥እኔ ልዘምር፥ልደሰት። ኢየሱስም ሆነ ሃዋርያቱ ስለነርሱ መባረክና መበልጸግ ሳይሆን በፍቅር ዓለምን ስለመቀየር፥ራስን መስዋዕት ስለማድረግ ነው ያሳዩን። ወደፊት በስፋት እንመለስበታለን።

ከወንጌል የፍትህ፥የጽድቅና የሰላም አጀንዳ ጋር ስለሚገናኘው የአሜሪካ አመራር ጉዳይ ልግባ።

የ Dec.19 የኤለክቶሬት ኮሌጅ ምርጫ ትረምፕን እንደሚመርጡ ዕድሉ የሰፋ ሲሆን ከዚያ ውጭ ይወስናሉ የሚለው በጣም አናሳ እንደመሆኑ ዳነልድ ትረምፕ ፕሬዚደንት ይሆናል ብለን በመውሰድ ልንጸልይለት ይገባል። ይሄንንም ባለፈው ጽሁፋችን መግለጻችን ይታወሳል።

ትረምፕ በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ጉዳይ ሃሳቡን በመቀየር እንደተቀበለውና ውርጃ የሚፈልጉ በሚፈቀድበት ስቴት እየሄዱ እንዲያደርጉ፥የመጓጓዣ ችግር ካለ ሁኔታው እንደሚታይ መናገሩን አካፍለናችኋል።

የትረምፕ ዋና አማካሪ ተደርጎ የተሾመው ፀረ ሴት፥ፀረ አፍሪካውያን፥ፀረ እስራኤልና ፀረ ኢሚግራንት እንደሆነ የሚነገረው ስቲቭ ባነን የነጭ ዘር የበላይነትን ለሚያስፋፉ ድርጅቶች መድረክ በመሆን ራሱም ሃሳቡን በማስፋፋት ይታወቃል። በቅርብ ቀን ኢሚግራንቶች ደህና ደህና ቦታዎችን ሁሉ ይዘውታል ይህ መቆም አለበት ብሏል። ከእንግዲህ ወዲህ ስራ በችሎታ ሳይሆን ቅድሚያ ለነጮች እንዲሰጥ ማለት ነው።አይሁዶችን አልወድም ብሎ እንደተናገረም ታውቋል።ለሴቶችና ለአፍሪካውያን የወረደ፥የንቀት አመለካከት እንዳለው ተረጋግጧል። ሴቶች በኢንተርኔት ትንኮሳ እየተደረገባቸው ነው ሲባል መፍትሄው ሴቶች ኢንተርኔት አለመጠቀም ነው ብሏል። 169 የኮንግረስ አባላት ስቲቭ ባነን ከነጩ ቤተ መንግስት ባስቸኳይ እንዲወጣ አሳስበዋል።

የሁለት መንግስታት መፍትሄ በሚለው ሃሳብ መሰረት ትረምፕ እራሱ እስራኤልንና ኢየሩሳሌምን ከፋፍሎ ግማሹን ለአረቦች መስጠት እንደሚፈልግ በቅርብ ቀን ፍንጭ አሳይቷል። 

ጌዮች ብዙ ገንዘብ ለትረምፕ የሰጡ ሲሆን ሪቸርድ ግረነል የትረምፕን ያህል ጌዮችን የሚወድና የሚደግፍ ማንም የለም ብሏል። የእነርሱን ባንዲራም ሲሰጠውና ትረምፕም ወደላይ ከፍ አድርጎ ሲያውለበልበው በቅርቡ ዓለም ሁሉ ያየው ጉዳይ ነው። ግረነል በዓለም መንግስታት የአሜሪካ ዋና አምባሳደር ይሆናል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ከፍተኛ ስልጣን በመያዝ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ጌይ ይሆናል።

ሌላው ለብዙዎች አሳሳቢ የሆነው የልጆቹና የአማቾቹ አራጊ ፈጣሪ የመሆን ስጋት ነው። ምንም የፖለቲካ ልምድ የሌላቸውና የአባታቸውን ትዕዛዝ የሚያስፈጽሙት የቤተሰቡ አባላት ጉዳይ ካሁኑ ችግር እየፈጠረ ሲሆን ታዋቂውና ተደናቂው የኒው ጀርዚ ገቨርነር ክሪስ ክሪስቲ በዚህ ምክንያት እንደተባረረ ታውቋል።

የዓለም ሁለተኛ ትልቁ ሀብታም ዋረን በፈት እንደ ትረምፕ ዓይነት ስሜታዊና ተበቃይ ሰው የኑክሌር ቦምብ በእጁ መግባቱ ከሁሉም በላይ ያሳስበኛል ብሏል። የዓለም መንግስታት አብዛኛዎቹ በከፍተኛ ስጋት ላይ ይገኛሉ። ሀገሮች የየራሳቸው ኑክሌር ቦምብ ቢኖራቸው ይሻላል ማለቱ የሚታወስ ሲሆን ገንዘብ ካልከፈላችሁን ወታደሮቻችንን ከዓለም ዙሪያ እናስወጣለን ማለቱ እንደ ራሽያ፥ሰሜን ኮሪያና ኢራን ላሉ ኑክሌር ቦምብ ላላቸው አገራት ጦርነት ለማስነሳት በር የሚከፍት አደገኛ አካሄድ ነው ተብሎ ተሰግቷል። አሜሪካ ለዓለም ሰላም የምታደርገውን በጎ አስተዋጽኦ ወደ ንግድ ሊቀይረው ነው የሚሉ እየተበራከቱ ነው።ከዚህ በተጨማሪ የሙስሊሞችን ቁጣ በማነሳሳት በአሜሪካ ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ አላስፈላጊ ፍጥጫና ጦርነቶችን የሚቀሰቅስ አዝማሚያ እያነሳሳ ነው ይላሉ። የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች አሁን በአሜሪካ የሚታየው የነጭ ዘር የበላይነት እንቅስቃሴ ወደ አውሮፓ ተዛምቶ በኢሚግራንቶች ላይ ከፍተኛ ችግርና ሁከት ያስነሳብናል ብለው ይሰጋሉ።የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት በመጀመሪያ ያስተላለፉት የአምባገነን ሀገር መሪዎች እንደሆኑ እየተዘገበ ነው። የራሽያ፥የሶሪያና የፊሊፒንስ መሪዎች ደስታቸውን ቀድመው የገለጹት ናቸው።መጀመሪያ በግንባር የተገናኙት የጃፓኑ ጠ/ ሚ አቤ ሲሆኑ ትረምፕ በምርጫ ዘመቻ የተናገረውን ከምር እንዳይወስዱት በአማካሪዎቹ ተነግሯቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትረምፕ ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ድርጊት ምክንያት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ከመታየቱ በፊት ትረምፕ ሰሞኑን ለከሳሾች 25 ሚሊዮን ዶላር በመስጠት እንዲሁም 1ሚሊዮን ዶላር ለኒው ዮርክ ከተማ ቅጣት በመክፈል ፋይሉ እንዲዘጋ አድርጓል።

ትረምፕ ነጋዴ እንደመሆኑ መጠን ንብረቱን በሙሉ ካልሸጠና ከንግዱ ዓለም ሙሉ ለሙሉ ካልወጣ (ለዚህም እስካሁን ፈቃደኛ አልሆነም) የጥቅም ግጭት ስለሚኖር ጉዳዩ ወደ ኢምፒችመንት፥ ከስልጣን የሚያወርድ ክስ ሊያደርስ ይችላል ሲሉ የህግ አዋቂዎች እየተናገሩ ነው።

አብዛኛው ነጭ ፕሮቴስታንት ትረምፕን የመረጠ ሲሆን አብዛኛው ላቲኖ፥አፍሪካን አሜሪካንና ኢሚግራንት ክርስቲያን ሂለሪን መምረጣቸው ታውቋል። በመላው ዓለም ያሉ አብዛኛዎቹ ወንጌላውያን አማኞችና መሪዎች በነጮቹ ምርጫ በመገረም ቅድስናን ያስተማሩን ሚሽነሪዎች እንዴት እንዲህ አደረጉ በሚል የአሜሪካን ክርስትና በመጠራጠር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።ጽድቅ የሚመጣው በወንጌል ስብከትና በፍቅር አገልግሎት እንጂ የአሜሪካ ቤተ ክርስቲያን ከፖለቲካ ሰዎች ለውጥ መጠበቋና በአንድ ሰው ላይ እንደዚህ መታመኗ ያሳዝናል፥ይህ የክርስቶስ መንገድ አይደለም ብለዋል።

ጥላቻና ዘረኝነት በኢሚግራንቶች ላይ መንግስታዊ ሊሆን ነው የሚሉ የተበራከቱ ከመሆኑም በላይ በመላው ሃገሪቱ ያሉ ኢሚግራንቶችና የመላው ዓለም ህዝብ በፍርሃት የተዋጠበት ጊዜ መሆኑ የብዙዎች እምነት ሆኗል።

ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው ጉዳዮች በፍትህ፥በፅድቅና በሰላም ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው። በተለይ ለአሜሪካ ሸክም ያላችሁ፥ በአሜሪካ በኩል መልካም ነገር ለዓለም እንዲተላለፍ ለምትፈልጉ ለመረጃና በዕውቀት ለመጸለይ እንደጠቀማችሁ እናምናለን።

ወደፊት ለአዲሱ ፕሬዚደንት አስተዳደር ለስደተኞች፥ለዝቅተኛ ገቢ ዜጎች፥ለኢሚግራንትና ለማይኖሪቲ መደረግ ስላለበት የሚጠቅሙ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ሃሳቦች ይዤ እመለሳለሁ።ባሉን ግንኙነቶች በአማካሪዎቹ በኩል ሃሳባችንን እናካፍለዋለን። እግዚአብሔር የድሆች አምላክ ነውና።

ማሳሰቢያ፥
ዶነልድ ትረምፕ ጌታ እንዲረዳው እንጸልይለት፥ወደ ራሱ ሃሳብ እንዲያመጣው።
እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ነው፤ሁሉን ለበጎ ይለውጠዋል፤
ወሬው ሁሉ የሚያስፈራ፥የሚሆነው ባለም ዙሪያ፥
እየከፋ ሲሄድ ጊዜው፥መሸሸጊያ ኢየሱስ ነው።

መንግስትና ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘተው ተነጋገሩ

pm-bp

ጠ/ሚ ሃይለ ማሪያምና የመድረክ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተገናኝተው መነጋገራቸው ታውቋል። ጠ/ሚኒስትሩ መንግስት ከመድረክ ጋራ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑን የገለጡ ሲሆን ፕሮፌሰር በየነም ለውይይቱ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸውላቸዋል። ይህ የሆነው ባለፈው ወር ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን እንዳልተገናኙና እየጠበቁ እንደሆነ የመድረክ መሪ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በውይይትና በመግባባት ነው። ውይይቱም ከአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ብቻ ከሚሆን በሀገር ውስጥም በውጭ ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ ጋር መሆን ይኖርበታል ብለን እናምናለን። ከእንግዲህ ሰው እንዳይሞት፥ ፍትህና ሰላም በኢትዮጵያ እንዲሰፍን እንፀልይ፥ድርሻችንንም እንወጣ።

የትረምፕ ፕሬዚደንትነት ገና አልተረጋገጠም፤የክሊንተን የመመረጥ ዕድል ሙሉ ለሙሉ አላበቃም

ማሳሰቢያ፤ይህ ጽሁፍ ለመረጃ፥ለዕውቀትና ለጸሎት ርዕስ እንጂ ማንንም ለመደገፍ ወይንም ለመንቀፍ የተጻፈ አይደለም።

“በሰው ልብ ብዙ አሳብ አለ፤ የእግዚአብሔር ምክር ግን እርሱ ይጸናል”ምሳሌ19:21
ምንም እንኳን ትረምፕ ምርጫውን አሸነፈ ቢባልም የአሜሪካ ህገ መንግስት ፕሬዚደንት እንዳይሆን የሚፈቅድ ቀዳዳ ይከፍታል። ኮንግረስ ፕሬዚደንቱን ኦፊሻሊ መርምሮ የሚያፀድቀው January 6, 2017 ነው። ከዚያ በፊት ኤሌክቶራል ኮሌጅ የተባሉት የየስቴቱ ተወካዮች December 19,2016 ኦፊሻሊ ምርጫ ያደርጋሉ። የፕሬዚደንቱ ሹመት ያኔ የሚወሰን ይሆናል።በዚሁ መሰረት እነዚህ የመጨረሻ ውሳኔ በዚያን ቀን የሚሰጡ ሲሆን ሃሳባቸውን መቀየር ይችላሉ።የሚያካሄዱትም የመጨረሻ ውሳኔ በስውር ድምጽ ስለሆነ የትረምፕ ፕሬዚደንትን ካልፈለጉ አብዛኛውን የህዝብ ድምፅ ያገኘችውን ሂለሪን መምረጥ ይችላሉ ወይም ለትረምፕ ድምጻቸውን በመንፈግና ቁጥሩን ከ 270 በማውረድ ኮንግረስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ይችላሉ።በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መራጮች ለተወካዮቹ ፔቲሽን እያስገቡ ነው።ባኦኪ ቩ የተባሉ የጆርጂያ ሪፓብሊካን የኤለክቶሬቱ አባል ለትረምፕ ድምፅ እንደማይሰጡ ከወዲሁ አሳውቀው ነበር፤ጥቂቶች እንኳን ባያጸድቁትና ከ270 ድምፅ በታች ከሆነ ኮንግረሱ የሚቀጥለውን ፕሬዚደንት በድምጽ ብልጫ ይወስናል። ምክትል ፕሬዚደንት ደግሞ በሴኔቱ ሊመረጥ ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ ዶናልድ ትረምፕ እስካሁን ያለባቸው የፍርድ ቤቶች ክስና ከባህሪያቸው አንጻር ካሁን በኋላም ሊፈጽሙት ከሚችሉት የህግ መተላለፍ አንፃር ወደ ኢምፒችመንት ወይም ከስልጣን የሚያስወርድ ክስ ነገሩ ሊሄድ ይችላል የሚሉ አሉ።
እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ማለትም የኤሌክቶራል ተወካዮች የDecember 19 የመጨረሻ ውሳኔና ከፕሬዚደንትነት ሊያስነሳቸው የሚችሉ ክሶች እድል አናሳ ቢሆንም የመሆን ዕድል አለው። እንዲያውም አንዳንድ ታዋቂ ተንታኞችና ሚዲያዎች የተወካዮችን ውሳኔ ቢያልፉም ተከሰው ስልጣን መልቀቃቸው አይቀሬ እንደሆነ በእርግጠኝነት ይናገራሉ።
ለሁሉም ህጉን ማወቁና ያለውን ሁኔታ በቅርብ መከታተል ይጠቅማል። የምንሰጣቸው አስተያየት፥ልንወስድ ያሰብናቸው እርምጃዎችና ውሳኔዎች፥እንዲሁም የምናደርጋቸው ጸሎቶች በዕውቀት ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል።

እግዚአብሔር አሜሪካንን ይባርክ

clinton-trump-whse

ሂለሪ ወይስ ትረምፕ?

ሂለሪ ወይስ ትረምፕ?
“ከእናንተ…ጥበበኞች አስተዋዮችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ።ዘዳግም1:13
trump-clinton
የዘንድሮ የአሜሪካ ምርጫ ፉክክር መከፋፋት የበዛበት፥ በክስና ስድብ የተሞላ ነበር። በዚህ ምክንያት በትምህርት ቤቶች እንኳ ለወትሮው የሚደረገውን ክርክሮችን ሰምቶ የቤት ስራ ለመስራት እስኪያስቸግር ድረስ ለልጆች የማይመች በጣም የወረደ ነበር። ያ ሁሉ አሁን አልፎ የምርጫው ቀን ሁለት ቀን ቀርቶታል። ባለፈው ለኦባማ እንደተደረገው ዘንድሮ ለማናቸውም የምርጫ ቅስቀሳ በኢትዮጵያውያን አልተካሄደም። ምናልባት አንዳቸውንም ለመምረጥ ፍላጎት ከማነሱ የተነሳ ሊሆን ይችላል። ዜግነት ያለው ሁሉ ቢመርጥ መልካም ነው፤አንዱ የዜግነት ሃላፊነት ነውና። የቀድሞው የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ዋና ጸሃፊ ኬንያዊው ሬቨረንድ ቱኩምቦ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ መጥተው እንዳሉት “የማይመርጥ ሰው የውሃውን ቁሻሻ ከምንጩ ከማድረቅ ይልቅ ቁሻሻውን ውሃ ለመጠጣት እንደመወሰን ነው”። የሰው ዲሞክራሲ ከእግዚአብሔር ሃሳብ ጋር ብዙ ጊዜ የማይገናኝ ቢሆንም በምድር ላይ ባለው አሰራር ለጊዜው ከዲሞክራሲ የተሻለ ሌላ አማራጭ ስለሌለ በዛ መስመር መሄዱ ግድ ነው። እግዚአብሔር ብቻውን ያለ ምርጫና ዲሞክራሲ የሚመራበት ስርአት ቲኦክራሲ ይባላል።ያ በዚህ ምድር አይሆንም በሚመጣው ዓለም እንጂ። ስለሆነም ለፍትህና ለብልጽግና የተሻለ የምንለውን በመምረጥ ድምጻችንን ማሰማት አለብን። በተለይ በአሜሪካ በክርስቲያንነት የተመዘገበው ህዝብ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ስለሆነ ከፍተኛ ተጽእኖ ማድረግ ይችላል። ይሄን ያወቁ ፖለቲከኞች ይህንን ድምጽ ለራሳቸው ለማድረግ የማይጥሩት ጥረት የለም። ክርስቲያኖች የሚወዱትን ጉዳዮች እናደርጋለን በማለት ለማማለል ይጠቀሙበታል እንጂ ብዙ ጊዜ ከልባቸው አይደለም። በዚህ ምክንያት ስልጣን ከያዙ በዃላ ቃላቸውን ሲሽሩ አይተናል። በመሆኑም ስንመርጥ ለጊዜው በቲቪ በምንሰማው ሳይሆን የተወዳዳሪዎችን ታሪክ ወደዃላ መለስ ብሎ በማየት የተሻለውን ማየት ያስፈልጋል። ዲሞክራሲ ማለት ከሁለት ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች መሃል ሻል ያለውን መምረጥ ማለት ነው።
አንዳንዶች ሂለሪ በኢሜል ጉዳይ ታማኝነት አጉድላለች፥ጉቦ ተቀብላለች፥ለሚያስወርዱና ለተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ነጻነት ትሰጣለች፥እንደወንጀል አታየውምበኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ በመግባት አድልዎ ታደርጋለች፥ከዲሞክራሲ ይልቅ የአሜሪካንን ጥቅም ታስቀድማለች፥ በፖለቲካ ዓለም እንደመቆየቷ ከወሬ በስተቀር ያመጣችው ለውጥ የለም፥ ከባሏ ቀጥሎ ስልጣን በመፈለግ ፕሬዚደንትነትን በቤተሰብ የሚወረስ የግል ንብረት አደረገችው፥በአክራሪ ሙስሊሞች ጉዳይ ለዘብተኛ ነች፥ስቴት ዲፓርትመንት በነበረችበት ጊዜ ለሞተው አሜሪካዊው አምባሳደርና አሁን ላለው ለሊቢያ ጦርነት ተጠያቂ ናትተወዳጅነትና የሚስብ ነገር የላትም ተብላ ትወቀሳለች። 
ሌሎች ደግሞ ትረምፕ ሴቶችን የሚያንቋሽሽና የሚንቅ፥አፉ በስድብና በነውረኝነት የተሞላ፥ግብር ላለመክፈል ቀዳዳ እየፈለገ የሚሸሽ፥ጥቁሮችን የሚጠላ፥ በገነባቸው ህንጻ ቤት እንዳይከራዩ የከለከለ ዘረኛ፥ ለድሆችና ለስደተኞች የማይራራ ጨካኝ፥የባለጸጎች ተከራካሪ፥ቶሎ የሚቆጣና ለመበቀል የማይመለስ፥ያልበሰለ ጥሬ ሰው ነው ብለው ይከሱታል።በውርጃና በግብረ ሰዶም ጉዳይ ለፖለቲካ ጥቅም ብሎ እንጂ ሃሳቡን በየጊዜው ይቀያይራል ስለዚህ ተግባራዊ አያደርገውም፥በኢትዮጵያ ጉዳይ ምንም እውቀት የለውም፥እንዲያውም ቡሽ በሴፕቴምበር አደጋ ጊዜ እንዳስወጣው የፓትሪዮቲክ ህግ ሪፐብሊካኖች ከዲሞክራሲ ይልቅ ለጸጥታ ቅድሚያ በመስጠት ስለሚታወቁ በኢትዮጵያ ያላቸው ፖሊስ የባሰ ይሆናል፥ለሙስሊሞች ሰብአዊ መብት ግድ የለውም፥ሁሉንም በሽብርተኝነት ያያል፥ ከራሽያ ጋር ባለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት የአሜሪካንን ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል፥አገሮች ሁሉ ኑክሌር ቦምብ እንዲኖራቸው ይፈልጋል ይላሉ።
ትረምፕ ካሸነፈ ምናልባት የመጀመሪያው ያለምንም ቀደምት የፖለቲካ ስራና ልምድ የተመረጠ የሚያደርገው ሲሆን ሂለሪ ከተመረጠች በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ የሴት ፕሬዚደንት ትሆናለች።
እንግዲህ ጸልየን ውስጣችንን ሰምተን የሚመስለንን እንምረጥ። እንደኛ ያልመረጡትን ሰዎች አናውግዝ፥በዚህ ምድር ፍጹም የሆነ ተወዳዳሪ የለም፥ሁሉም በታየውና በደረሰበት ነው የሚመላለሰው። እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፥ላለመስማማት ተስማሙ።እግዚአብሔር አሜሪካንን ይባርክ።