
የአስተዳደር ታሪካችን ብዙ ውጣ ውረድ የበዛበትና በከፍታና በዝቅታ ያለፈ ሲሆን በዚህ ሁሉ ግን ኢትዮጵያዊነት ገንኖ እና ሁሉን አሰባሳቢ ሆኖ ቆይቷል።
መስራችና ዳይሬክተር


የአስተዳደር ታሪካችን ብዙ ውጣ ውረድ የበዛበትና በከፍታና በዝቅታ ያለፈ ሲሆን በዚህ ሁሉ ግን ኢትዮጵያዊነት ገንኖ እና ሁሉን አሰባሳቢ ሆኖ ቆይቷል።
ሰሞኑን ከሚፈቱት እስረኞች መካከል ምህረት አይደረግላቸውም ተብለው የሚገመቱት፥ በፓርላማ አሸባሪ የተባሉት የግንቦት7 እና የኦነግ አባላት እንደሚኖሩበት አውቀናል። ከዚህ በተጨማሪ ይቅርታ እንዲጠይቁ አልተገደዱም። ይህ በእውነት ወደፊት ሊካሄድ ለሚችለው ብሄራዊ መግባባት ትልቅ ተስፋ ነው። ትጥቅ ያነገቡ ሁሉ የሀገራዊው ውይይትና ምክክር ብሎም ድርድር አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ ይሰጣል። ይህ ደግሞ በተለይ በሰላምና መግባባት ላይ ለምንሰራ ሁሉ ተስፋ ፈንጣቂ ነው። እግዚአብሄር ለሀገራችን ሰላምንና ፍትህን ያምጣልን።
መርዶክዮስ ፍትህ አጣ፥አስቴር ጾም ጸሎት አወጀች፥ከዚያስ ምን አደረገች?
ሀገራዊ ጥሪ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች
ብዙ ወገኖች የአስቴርን የሶስት ቀን ጾም ጸሎት ምሳሌ በማድረግ በተለያዩ አርዕስት ላይ ጾም ጸሎት ይይዛሉ። በቅርቡም ለሃገር እንደተጸለየ ተገንዝቢያለሁ። መልካም ነገር ነው።ጸሎት ሁኔታዎችን ለእኛ ይቀይራል ወይ እኛን ለሁኔታዎች ይቀይራል።አስቴር በመጸለይዋ ወደ ንጉሱ ለመግባት ድፍረት አገኘች፥ጥበብ ሆነላት፥ሞገስም ተላበሰች።ጸሎት የሁሉ ነገር መነሻ ነው። ያለጸሎት ምንም ነገር አይሆንም።
የብዙ ክርስቲያኖች ችግር የሚጀምረው ግን እዚህ ጋር ነው።ጸሎት ላይ ያቋርጣሉ፥ ወደሚቀጥለው ደረጃ ከፍ አይሉም።
አስቴር ከጸለየች በኋላ ግን በጸሎቷ ረክታ አልተቀመጠችም። ቃሉ እንደሚለው ያለ ህግ ቢሆንም ወደ ንጉሱ ገባች፥ንጉሱ ቢቆጣም፥ቢገድለኝም ብላ ሳትፈራ ለመርዶክዮስና ለህዝቧ ፍትህ ልትጠይቅ ወደ ንጉሱ ገባች። ሞገስ አገኘች፥ንጉሱ ተቀበላት። በድፍረትም አንደበትዋን ከፍታ የህዝቧን ብሶት ተናገረች። ሁለት ጊዜ ስብሰባ በቤትዋ አዘጋጅታ ንጉሱንና ሊያጠፋቸው የተነሳውን ሀማን ጋበዘች።
በዚህ ጊዜ ሌላ ነገር ተከሰተ። ንጉሱ መዝገብ ይምጣልኝ ብሎ ፍትህ አጥቶ ሊገደል የነበረውን የመርዶክዮስን ገድል የሚያወራ ታሪክ ወጣ። አያችሁ መርዶክዮስ በደህና ቀን በጎ ስራ ሰርቶ ነበር። በንጉሱ ላይ ሊሰራ የነበረውን ግፍ አጋልጦ ነበርና ያ ተቆጠረለት።በሞት ፈንታ እንዲከብር ተደረገ። አስቴር በግብዣዋ ላይ ሞት ያወጀባቸውን የሀማን ግፍ ለንጉሱ ተናግራ ፍትህ አስገኘች። በአስቴር ሪፖርትና በወቅቱ ሀማ ከድንጋጤ የተነሳ የማይሆን ነገር አድርጎ ነበርና ንጉሱ ተቆጥቶ በሞት እንዲቀጣ አስደርጎ አስቴርና የአይሁድ ህዝብ በግፍ ከመገደል ተረፉ፥ፍትህ አገኙ።
ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? ከጸሎት በኋላ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል።አስቴር ጸልያ ብትቀመጥ ምንም አይሆንም ነበር። መርዶክዮስም በደህና ጊዜ በጎ ስራ ባይሰራ ኖሮ ፍትህ አያገኝም ነበር።
እባካችሁ ክርስቲያኖች፥ ጸልየን ቁጭ አንበል፥እንደ አስቴር እንውጣ፥ወደ ንጉሱ እንሂድ፥ለህዝባችን ፍትህ እንጩህ፥ብጠፋም ልጥፋ ብላ ነው የሄደችውና አትፍሩ፥ጌታ ሞገስ ይሆናችኋል።
በኢትዮጵያ ያላችሁ ክርስቲያን ወገኖቼ፥ወደ ከተማችሁ መሪዎች ሂዱ፥ስለ ፍትህ
ተሟገቱ፥አትፍሩ፥እውነትን በፍቅር ተናገሩ። እንደ ዳንኤል ለናቡከደነጾር ምክርን ምከሩ፥እንደ ዮሴፍ ለፈርኦን ጥበብን አውጁ፥ በዓለም ካለው በእናንተ ውስጥ ያለው ይበልጣልና። በአገልግሎታችን ብዙ ጊዜ ወደ መሪዎች እየገባን ስለሰላምና ፍትህ እንናገራለን፥ወደፊትም እንቀጥላለን።
ጌታ በባለስልጣኖች ፊት እንደ አስቴር ሞገስ ይስጣችሁ።መርዶክዮስም ፍትህ ያገኛል፥ከመሞትም ይተርፋል። ሞት በሃገራችን ይብቃ፥ አለአግባብ እስራት ይብቃ፥ኢፍትሃዊነት ይብቃ፥የሰብአዊ መብት ረገጣ ይብቃ፥የሰላምና የፍትህ አምላክ በኢትዮጵያ በክብር ይገለጥ፤አሜን።
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ አገልግሎት
ethiopiariseandshine.com
ሬቨረንድ ሳሙኤል ሮድሪጌዝ የአሴምብሊስ ኦፍ ጋድ ፓስተርና የ16 ሚሊዮን ላቲኖ ክርስቲያኖች ህብረት ፕሬዚደንት ነው።ለእኔም ወዳጄ ነው። በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ አብረን ተካፍለናል።ፕሬዚደንት ትረምፕ ስልጣን የያዘ ቀን ስነ ስርዓቱን በፀሎት እንዲመራም መርጦት ነበር።የሳም መርህ ወንጌል ስርጭትን እንደ ቢሊ ግራሃም፥ ፍትህን እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ይዘን መሄድ አለብን የሚል ነው። አሁንም ድረስ የትረምፕ አማካሪ ፓስተር ነው። ሰሞኑን ፕሬዚደንቱ በአፍሪካ ጉዳይ ተናገረ በተባለው ላይ የሚከተለውን ብሏል፥
“ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠረው፤ያለ ምንም ልዩነት። ስለሆነም ኢሚግሬሽንን በተመለከተ ሁሉም ሰው ህጉን ተከትሎ መብቱ እንዲጠበቅ ያስፈልጋል።ከናይጄሪያም ሆነ ከኖርዌይ፤ከሆላንድም ሆነ ከሄይቲ እሴታችንን እስከተቀበሉና ሸክም ሳይሆኑ ለሀገራችን ተጨማሪ ግብአት እስከሆኑ ድረስ እኩል መስተናገድ አለባቸው።ከዚህ በተጨማሪ ግን ከታላቅ አክብሮት ጋር የምናገረው ፕሬዚደንቱ አሉ የተባለው ነገር በመጨረሻው ጥሩ እይታ እንኳን ብናየው ሊባል የሚችለው የተሳሳተ፥የማይገባና ጎጂ አስተያየት መሆኑን ነው።ለምን? እግዚአብሔር እነዚህን ሀገሮች ሲያይ እንደ ልጆቹ ነውና የሚያያቸው።”
ከጥቂት ጊዜ በፊት ከኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት መሪዎች አንድ ነገር ሰማሁ ስለ አቶ በቀለ ገርባ።ውይይታችን በወቅቱ የኢትዮጵያ ጉዳይና በአገልግሎታችን ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ስለምናካሂደው የሰላም ጥረት ነበር። ስለ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ስንነጋገር ነው እንግዲህ የአቶ በቀለ ጉዳይ የተነሳው። አቶ በቀለ የወንጌል አማኝ እንደሆነና በግል እንደሚያውቁት አንድ የአብያተ ክርስቲያናቱ መሪ ነገሩኝ።ሲቀጥሉም በጣም የተወደደ ሰላማዊና ታማኝ አማኝ እንደሆነ በፍጹም በሌላ ነገር እንደማይሰማራ አረጋገጡልኝ። እንዲያውም ማንም ሰው ስለርሱ ማንነት መረጃ ቢፈልግ የኛ ቤተ ክርስቲያን አባል ነውና መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ አሉኝ።
በነገራችን ላይ በሌላ ጊዜ ከዶክተር መረራ ጋር ስንጫወት በኛ ፓርቲ ውስጥ እንደ በቀለ ገርባ በሰላማዊ ትግል የሚያምን የለም፤እንደውም የማርቲን ሉተር ኪንግን ነውጥ አልባ መጽሃፍ በኦሮምኛ የተረጎመ ነው ያሉኝን አስታውሳለሁ።የመጽሃፉ ስም “ህልም አለኝ” የሚል ነው።
በቅርቡ እንደተረዳሁት የአቶ በቀለ ክስ ከሽብርተኝነት ወደ ተራ የወንጀል ክስ ወርዷል። ይህን ታዋቂና ብዙ ደጋፊዎች ያሉትን ሰው እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች መፍታት ለብሔራዊ መግባባት የራሱን ሚና ይጫወታል ብለን እናምናለን። በዶክተር መረራ የተጀመረው በጎ እርምጃ በዚሁ ይቀጥል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።