እውነትን ወይስ ፍቅርን…የትኛውን?

እውነትን ወይስ ፍቅርን…የትኛውን?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶሻል ሚዲያ በተለይም በፌስቡክ የሚታይ ሚዛን ያለመጠበቅ ነገር አለ።ወደ አንድ ጫፍ መስፈንጠር ይበዛል። አንድ ትክክለኛ ነገር ያዝን ማለት በሁሉም ትክክል ነን ወይም ሚዛን የጠበቀ አካሄድ ነው ማለት አይደለም።
በፌስቡክ የሚታየውን ፈር የለቀቀ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት “ፌስዳቢዎች” እንደተባሉ ሰምቻለሁ። የፌስቡክ ተሳዳቢዎች ማለት ነው። ይህ ደግሞ የሚታየው በሁሉም ጎራ ነው። በተለያዩ ሃይማኖቶችና ቤተ እምነቶች እንዲሁም በፖለቲካው መድረክ አካባቢ ጭምር።ልዩነቱ እስከማይታወቅ ድረስ በእግዚአብሔር ስም የሚሰዳደቡት ከፖለቲካው ያልተለየ ሆኗል። ይህ ምን ማለት ይሆን? በአንድ አጀንዳ ላይ አሸናፊና ትክክል ሆኖ ለመውጣት እግዚአብሔርን ማሰደብና ጥላቻን በመዝራት ከወንድምና እህታችን ጋር ያለውን የፍቅርና የመከባበር መስመር መቁረጥ ምን ይባላል? የወንጌል ዓላማ ሰውን ማዳን ነው ወይስ በኔ መንገድ ካልሄድክ ገፍቼ እጥልሃለሁ ነው?
ጳውሎስ “ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” ሲል እኮ ከመሸናነፍ መንፈስ አልፈን ፉክክር ወደሌለበት ከፍ ያለ አድማስና ልምምድ ውስጥ ነን ማለቱ እኮ ነው።
ለሀገርስ ቢሆን ከራስህ ዜጋ ጋር መጠላላት ምን ይፈይዳል? ነገ እኮ ልትዋለድ ትችላለህ፤ወደኋላ ብትቋጠርም ይሄኔ ዘመድ ትሆናለህ።ወዳንተ ሃሳብ ሰው እንዲመጣ ከፈለክ በምን ሂሳብ ነው ስድብ የሚያመጣው? ወይስ በተስፋ መቁረጥ አጥፍቶ መጥፋት መሆኑ ነው?
መጽሃፍ ቅዱስ በኤፌ4:15 “እውነትን በፍቅር እየያዝን” ይላል። በአንዳንድ ትርጉሞች “እውነትን በፍቅር በመናገር” ይላል።
አንዳንድ ወገኖች እውነትን ስለያዝኩ መቆጣት፤ማውገዝ፤መዝለፍ መብቴ ነው ይላሉ።
ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው እኔ ምን አገባኝ፤ከሰው ጋር በፍቅር አርፌ ለምን አልኖርም፥ምን አጋጨኝ? ይላሉ፤ስህተትን እያዩ ዝም ይላሉ።
እንግዲህ እዚህ ጋር የምናየው ሁለት በተለያየ ጎራ ያሉ ወገኖችን ነው።ሁለቱም ጋር የተወሰነ ትክክል የሆነ ነገር አለ፤ሁለቱም ግን ለጥጠውት መጠኑን አልፈዋል። እንግዲህ እዚህ ጋር ነው “እውነትን በፍቅር” የሚለው የሚገባው፤ሚዛናዊነት የሚገባው እዚህ ጋር ነው ማለት ነው።
እውነት ወሳኝ ነገር ነው። ነጻ የሚያወጣው እውነት ነው፤መፍትሔ የሚሆነው እውነት ነው።
እዚህ ጋር ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፤እውነት ያለው ማን ጋር ነው? የትኛው ጎራ ነው እውነቱ ያለው? በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ከታሪክም ሆነ ከገሃዱ ዓለም የምናየው እውነትን ይዘናል የሚሉ አብዛኞዎቹ እንዳልያዙት ነው።አይ እኔ የተለየሁ ነኝ እኔ ጋር ያለው በእርግጥም እውነት ነው፤ማስረጃውም ይሄ ይሄ ነው እንላለን።አንዳንዴ ያ ነገር ትክክል ቢሆንም ብዙ ጊዜ ሙሉ እውነት ላይሆን ይችላል። ግማሽ ብርጭቆ ውሃ ያዩ ሁለት ሰዎች ተቃራኒ የሚመስል ግን እውነት የሆነ ነገር ሊናገሩ ይችላሉ። አንዱ ብርጭቆው እኮ ግማሽ ባዶ ነው ብሎ እዚያ ላይ ሲያከር ሌላው ደግሞ ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ እኮ ነው ብሎ ሊጮህ ይችላል።
ሁለት ዓይነ ስውራን ዝሆንን ሲያዩ አንዱ እግሩ አካባቢ በመዳሰስ የዝሆኑ አካል ያ ብቻ ሊመስለው ይችላል፤ሌላው ደግሞ ሌላኛውን አካሉን በመዳሰስ ዝሆን ማለት እርሱ የዳሰሰው ብቻ ሊመስለው ይችላል።
“ከዕውቀት ከፍለን እናውቃለን” ይላል ጳውሎስ።ስለዚህ እውነትን አውቄ ጨርሻለሁ ከማለት ይልቅ የደረስኩበት ይሄ ነው በማለት በትህትና ማስረዳትና የሌላውን ሃሳብ ማክበር አስፈላጊ ነው።ጥልቅ በሆነው በመንፈሳዊና በዶክትሪን ጉዳይ እንኳ ብዙ የምናከብራቸው አብያተ ክርስቲያናትና መሪዎች አይስማሙም። በጥቅሱ ላይ ሳይሆን በትርጉሙ ስለሚለያዩ የየራሳቸው እውነት የሚሉት ትርጓሜ አላቸው። በመሆኑም ትሁት መሆንና ምናልባት እኛ ከምናውቀው ሌላ ተጨማሪ ዕውቀት ካገኘን ተወያይቶ፥ጥያቄ ጠይቆ አቋምን ለመቀየር እንኳ ዝግጁ መሆን አለብን።
“የትም ብትወስደኝ እውነትን እከተላለሁ”፤ በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበት ይሆናል።
ስለዚህ ከምናውቀው የማናውቀው ስለሚበልጥ ለጠብና ለጥላቻ ራሳችንን አናጋልጥ።የደረስንበትን ግን ያለፍርሃትና ማመቻመች እናስረዳ።
ሌላው ፍቅር የሚለው ቃል ነው።ዋው፥ከዚህ የበለጠ ቃል በዓለም ላይ አለ? ተነግሮም ተጽፎም የማያልቅ ከውቅያኖስ የበለጠ ጥልቅ የሆነ የዓለማችን ታላቁ ስጦታ።
ወንጌል “ከሁሉ የሚበልጠው ፍቅር ነው” ይላል።አንድ የብሉይ ኪዳን ሊቅ እንዲህ አለ “የመጽሃፍ ቅዱስ ዋናው መልዕክት አምላክህንና ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ ነው።ሌላው ሁሉ የዚህ ትዕዛዝ ማብራሪያ ነው”። ኢየሱስም “ከትዕዛዛቱ ሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፥ህግም ነቢያቱም በዚህ ተሰቅለዋል” ብሏል። የወንጌል ማዕከላዊ ጥቅስ የሚባለው “ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና” የሚለው ቃል ነው።
ሰዎች ተዋደው ተጋብተው የሰውን ዘር እንዲተኩ አምላክ ያዘጋጀው መንገድ፥የመኖራችን ምክንያት። የእናት ፍቅር፥የልጅ ፍቅር፥ የወዳጅ ፍቅር፥ የሀገር ፍቅር ወዘተ ባጠቃላይ የህይወታችን ትርጉም ፍቅር ነው።የቃሉን ፊደላት ስንከፋፍል ፍጽምና፥ቅድስና፥ርህራሄ ብዬዋለሁ። ለፍቅር የሚከፈል ዋጋ አይቆጭም። ከመጽሃፍ ቅዱስ ተወዳጅ ምዕራፎች አንዱ 1ኛ ቆሮንቶስ13 ነው።የፍቅር ምዕራፍ ይባላል። እውነትን ያለፍቅር ብንናገር ማን ይሰማናል? መሬት እንኳ ተቆፍራ ካለሰለሰች ፍሬ አትሰጥም።ሴት ልጅን በፍቅር ካልቀረብን የጥቅስ ጋጋታ ብቻ ለትዳርና ለግንኙነት አይማርካትም።
ኢየሱስ “እግዚአብሔር የሚመለከው በእውነትና በመንፈስ ነው” አለ።ምን ማለት ነው? እውነት አይበቃም፥መንፈስ ያስፈልጋል፥ያም ማለት እውነትን የሚያለሰልስ፥በቀላሉ እንዲፈስ፥ተቀባይነት እንዲያገኝ፤ለሰዎች እንዲበራ የሚያደርግ መንፈሱ ነው። ፍቅር ደግሞ አንዱ የመንፈስ ባህርይ ነው። ስለዚህ እውነት ብቻ ይዞ መሄድ ባልተቆፈረና ባለሰለሰ መሬት ላይ እንደመዝራት፥ሴትን በንግግር ብቻ ለማሳመንና ለማግባት እንደመሞከር ማለት ነው።አይቻልም፥አይሆንም፥ፍሬ አያፈራም፥እውነትን በፍቅር!
በፌስ ቡክ ያለው ደረቅ ክርክርና ጥላቻ ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገር መፍትሔ አያመጣም።

ፌስዳቢዎች አስተውሉ።እድሜያችሁን በከንቱ አትጨርሱት። ለተቺና ለተሳዳቢ የተጻፈ ታሪክም ሆነ የቆመ ሀውልት የለም።ትረሳላችሁ።መረሳት ብቻ ሳይሆን ለልጅ ልጆቻችሁ የሚተርፍ መጥፎ ሌጋሲ፤አሻራ ትታችሁ ትሄዳላችሁ። የተነጋርነው ሁሉ በአምላክ ፊት የሚያስጠይቀን ሲሆን በዘመናዊ ቴክኖሎጂም ቢሆን ሬከርድ ስለተደረገ ብትጸጸቱ እንኳ ለዘላለም ታሪክ ሆኖ ስማችሁን ያጎድፋል።
ባልና ሚስት እውነት እውነት ብቻ ቢሉ አንድ ቀን አብረው መኖር አይችሉም።ለሰላምና ለፍቅር ሲሉ እየተሸናነፉ ነው።
ቤት በግ የሆነ ሰው ፌስ ቡክ ላይ አንበሳ ሲሆን ደስ አይልም።
በመጨረሻ ማለት የምፈልገው እውነትን በፍቅር ተናገሩ። እውነት መሆኑን አረጋግጡ፥ለመማማር ቦታ ይኑራችሁ።
ስለ ፍትህና ሰላም ተናገሩ፥እውነት ነውና፤ስለ ወንጌል ተናገሩ፥ እውነት ነውና። ሁሉ ግን በፍቅር ይሁን።
አንድ የጥንት መነኩሴ ባለው ልዝጋ፥
“በመሰረታዊ ነገሮች አንድነት፥
መሰረታዊ ባልሆኑ ልዩነት፥
በሁሉም ግን ቸርነት።

Reverend Daniel Tassew

Advertisements