አስቸኳይ ጥሪ

October 5, 2016

የሀገራችን ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ነው። ባለፈው እንደተናገርነው ፍትህ ካልሰፈነና የህዝቡ ጥያቄ ተመልሶ ከተቃዋሚዎች ጋር አስቸኳይ ንግግር ካልተጀመረ የሰዎች መሞት እየቀጠለ ነው።ከኢሬቻ በኋላ እንኳን በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተነሳው ግጭት ሰዎች እየሞቱ ነው።
“የሟቹን ሞት አልፈቅድም ይላል እግዚአብሔር”።
ብዙ ሰዎች አክራሪ አቋም ውስጥ ገብተዋል፤ምሬትና እልህ ተባብሷል። በደጋፊም በተቃዋሚም ወገን ያሉ አንዱ አንዱን ለማሸነፍ፥ለማስወገድ እንጂ አብረን እንዴት እንኑር የሚል ሃሳብ ቀርቷል። ሰላማዊ መፍትሄ የምንል ሰዎች ድምጻችን እየተዋጠ “ፍለጠው ቁረጠው” እየገነነ ነው።ይህ ለሃገራችን ያዋጣል? ማንም ላይ ለመፍረድ አይደለም፤በሁለቱም ጎራ ያሉት ከመረዳታቸውና ከብሶታቸው በመነሳት ነው። በ21 ኛው ክፍለ ዘመን እየኖርን መነጋገር አለመቻል አግባብ አይደለም። የሰዎች መሞት መቆም አለበት፥የጥላቻ ዘመቻ መቆም አለበት፥ውይይት መጀመር አለበት።ቫክላቭ ሃቨል የተባለ ሰው “አመጽ አልባ ትግል የመረጥነው ቅዱስ ለመሆን ፈልገን ሳይሆን ማሸነፊያው መንገድ እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው፤በአመጽ ከሄድን እንሸነፋለን” ብሏል። መገዳደል ሁኔታውን ከማባባስና የማይረሳ ቂምና ቁርሾ ከማስቀመጥ በቀር አንድ ድርጅት እንኳ ቢያሸንፍ ሌሎቹ ድርጅቶች ትግላቸውን ስለሚቀጥሉ በመሃል ኢትዮጵያ ትሸነፋለች።
ሰሞኑን የነፃ ኦሮሚያ የሽግግር መንግስት አዘጋጅ ተቋማትና ወታደራዊ ክንፍ እንደሚቋቋም ተሰምቷል። በኢትዮጵያ ጦር ባሉ ከአስር አለቃ እስከ ጄኔራል የውስጥ አርበኛ የሰራዊት አባላትና 500,000 (አምስት መቶ ሺ) በሚሆን መሳሪያ የታጠቀ የኦሮሞ ህዝብ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንደሚጀመር ይፋ ሆኗል። ወዴት እየሄድን ነው? ሶስት ነገር ለማሳሰብ እንፈልጋለን፥
1-ጸሎታችንን አጠናክረን እንቀጥል፤”በመንፈሴ እንጂ በሃይልና በብርታት አይደለም ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ወደ እኔ ጩህ እኔም አመልስልሃለሁ፤አይተህ የማታውቀውን ታላቅና ሃይለኛ ነገርም አሳይሃለሁ፤ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለምና”።
2-የሃይማኖት መሪዎች፥የሃገር ሽማግሌዎች፥የሚመለከታችሁ ሁሉ ውይይትና ድርድር ባስቸኳይ እንዲጀመር ዛሬ ነገ ሳትሉ ጥረታችሁን አጠናክሩ።
3-ሌሎቻችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በጥላቻና በበቀል ፈንታ ፍቅርንና ፍትህን እንስበክ። ሁለቱን ሚዛን ማድረግ ቀላል አይደለም፥አንዱን ስትይዙ አንዱ ያፈተልክባችዃል።ለእግዚአብሔር ግን ሁሉም ይቻላል።
እባካችሁ ድርሻችሁን ተወጡ፤ይህን መልእክት ሼር በማድረግ አሁንም ጥላቻን እናሸንፍ፤አዎ፥በመጨረሻ ፍቅርም ፍትህም ያሸንፋሉ! አሜን

Advertisements

መጪው አደጋና መፍትሄው

Oct 3, 2016

mourning

በትናንትናው ዕለት በደብረ ዘይት ቢሾፍቱ የደረሰው እጅግ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው። በበርካታ ቤተሰቦች ዛሬ ሃዘን አለ፤ድንኳኖች ተጥለዋል፥የቀብር ስነስርዓቶች ይፈጸማሉ፤የሟች ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ዘመድ አዝማድ ጎረቤት ወዳጅ ሁሉ በዚህ ጉዳይ ተጎድቷል። እነዚህ ወገኖች ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ በመሆናቸው ሀዘኑ አገር አቀፍ ነው።ባጠቃላይ በሀገር ውስጥም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህ አደጋ አሳዝኖታል፥አንገብግቦታል፥አሳስቦታል፤ ይህ ብቻም አይደለም የሀገሪቱ ጉዳይ ወዴት እየሄደ ነው፥ከኔ ምን ይጠበቃል? የሚል ጥያቄ በውስጡ ይጭራል። እስካሁን የጉዳዩ አሳሳቢነት ገብቷቸው ከጸሎት ጀምሮ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ያሉ ወገኖች ቢኖሩም የአሁኑ ክስተት እነርሱም ጥረታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ፥ሌሎች ከዳር ቁጭ ብለው የሚታዘቡ ደግሞ በሀገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚገፋፋ ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ዛሬ ለጎረቤታችን ራርተን መፍትሄውን በጋራ ካልፈለግን ነገ የኛንም በር ማንኳኳቱ አይቀርም፤እስካሁን ካልተንኳኳ ማለቴ ነው።
ጉዳዩን በቅርበት ለምንከታተል የትናንቱ የኢሬቻ አደጋ የሚያሳዝን ቢሆንም የማይጠበቅ አልነበረም። በህዝቡ ዘንድ ያለውን ቁጣና ተስፋ መቁረጥ ያየ ሰው እንዲያውም ከዚህ በላይ ለሀገሪቱ ህልውና አደጋ የሆኑ ከፍተኛ ችግሮች እንዳይነሱ ያስፈራል።ምን አልባት የትናንቱ እንደ ትንሽ ነገር የሚታይበት ሁኔታ ማለት ነው። ኢቢሲ የትናንቱን ክስተት ጸረ ሰላም ሃይሎች ያነሳሱት ሲል ሪፖርተር ጋዜጣ ከስፍራው ሆኖ እንደዘገበው የህዝብ ተቃውሞ ብሎታል። የህዝብን ተቃውሞ የጥቂቶች ካደረግነው መፍትሄ አይመጣም።
ባለፈው ያቀረብናቸው 7 የመፍትሄ ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፥
1-በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ እንዳይፈጸም እንጠይቃለን።
2-ያልተመጣጠነ ሃይል በመጠቀም በሰልፈኞች ላይ ግድያ የፈጸሙ ወገኖች በአስቸኳይ በህግ ይጠየቁ፤ይሄንንም የሚያጣራ ገለልተኛና በሁሉም ወገኖች ተኣማኒነት ያለው አጣሪ አካል ምርመራውን ያድርግ፤
3-ከተቃውሞ ጋር በተያያዘ ያላግባብ የታሰሩ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት በወህኒ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች መንግስት ለሰላምና ለመግባባት ሲባል ይፍታ። የእስረኞች ሰብዓዊና ህገመንግስታዊ መብቶቻቸው ተጠብቀው ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸው ጋር ያለምንም ተጽዕኖ ይገናኙ፤ፍርድ ቤት የመቅረብ መብታቸው ይጠበቅ፤
ፍርድ ቤቶች ከማንኛውም የፖለቲካ ተጽዕኖ ነፃ ሆነው ፍትህን ይስጡ።
4-ህዝቡ ያቀረበው የፍትህ ጥያቄ በአስቸኳይ ተገቢው ትኩረት ይሰጠው፤ጥያቄዎቹም ይመለሱ።
5-በተለያዩ ወገኖች ያለውን ቁጣ የምንረዳ ቢሆንም ከጥላቻ ንግግሮችና ከዘር ተኮር ስድቦች ከጥቃትና ከሀይል ተግባሮች ሁሉም አካል እንዲቆጠብ እናሳስባለን።እንዲህ አይነት ነገር ሀገር የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ ነው። ስሜታችንን ተቆጣጥረን የወደፊት ሀገርን አንድነትና ህልውና ማስጠበቅ መቻል አለብን። እድሉ ያለን ዛሬ ነው። አንዴ ጥላቻው ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ መመለሻ አይኖረውም።
6-ይህ ችግር እንዳይደገምና ሀገሪቷ ወደ ለየለት ሁከት እንዳትገባ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በተወካዮቻቸው የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ይዘጋጅ፤ይህን ውይይት የሚያመቻች ሁሉም ወገን የሚቀበለው ከሀገር ውስጥና አስፈላጊም ከሆነ ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የተውጣጣ አካል ባስቸኳይ ይቋቋም። የወደፊቱም የሀገሪቱ አቅጣጫ መግባባትና በልዩነት አንድነት በሚፈጠርበት ሁኔታ ላይ ተመሳሳይ ብሄራዊ መረዳት ላይ ይደረስ።ለዚህም ያለ ማንም የፖለቲካ ተጽእኖ በተለይ የሃይማኖት መሪዎች፤የሀገር ሽማግሌዎች፤የሲቪክ ድርጅቶችና አስፈላጊ ከሆነ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ድጋፉን ያድርግ።
7-ከዚያ በመቀጠል የሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉን ያሳተፈና በተቃዋሚውም በዓለም አቀፍ ደረጃም ተኣማኒነት ያለው ይሁን።
እነዚህ ከላይ የዘረዘርናቸው ካልተደረጉ ወዳልታሰበና አላስፈላጊ ክስተት ነገሩ ሄዶ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ያሰጋል።አንዳንዶች ሰላማዊ ውይይት ካሁን በኋላ አይሰራም፥አመጽ ብቻ ነው መፍትሄው ይላሉ።እኛ ግን እንደ ሰላም መልእክተኞች የሰው ነፍስና የሀገር ሀብት እንዳይጠፋ በሰላማዊ መፍትሄ ተስፋ አልቆረጥንም። ኢህአዴግ በመግለጫው አንድ ነገር ብሏል፥ ለለውጥ ስለሚያነሳሳን ህዝቡ ሰላማዊ ተቃውሞውን፥ትግሉን ይቀጥል ብሏል። መንግስት ላይ ህዝቡ ሰላማዊ ግፊቱን በመጨመር ህዝቡ ራሱ በመረጠው መንገድ መመራት ይኖርበታል ብለን እናምናለን።
እግዚአብሔር የሟች ቤተሰብ ያጽናናልን።

ዳንኤል ጣሰው