“ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሳሁ፤ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?” “እንቆቅልሼን ፍታ፥ላንተ የሚያቅትህ የለም ጌታ”

isis crisisMartyrs Reward - 1

በጦርነት ያሳለፍነው ዘመን፣ በድህነት የተሰቃየነው፥በሽታ የጨረሰው ህዝባችን፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በስደት የሚሞተው የሚሰቃየው፥አውሮፓ ባህር፥በየመን፥በሳውዲ አረቢያ፥በደቡብ አፍሪካ፤ጭራሽ የባሰ ደግሞ መጣ። እርግጥ ብዙዎች የአይሲስ ሰለባ ቢሆኑም የኛ ግን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው።
“ወደጌታ ልሄድ እናፍቃለሁ፥ከሁሉ የሚሻል ነው፤በስጋ መኖሬ ግን ለናንተ የሚያስፈልግ ነው።” በዚህ አለም መኖር ትርጉም የሚሰጠው ለሌሎች ከኖርን ነው።ለተበደሉ ፍትህ፥ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ስንሆን።ደስተኛ መሆን ከፈለክ ሌሎችን ደስ አሰኝ።አሁን ካልተነሳን መቼ? እኛ ካልሆንን ማን?
ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉን የሚንቀሳቀስ ነገር ሁሉ አንቀሳቃሽ አለው።ጉዳያችንን ራሳችን ካላንቀሳቀስን ዘላለማዊ እንቆቅልሽ ሆኖ ይቀራል።ጸሎት መልካም ነው፥ዋናም ነው፤ “እንቆቅልሼን ፍታ፥ላንተ የሚያቅትህ የለም ጌታ”፤ ማለትም አግባብነት ያለው ተማጽኖ ነው። ግን እዛ ላይ አይቆምም።በምድር ላይ ስንኖር ምድራዊ ህጎችን መከተል አለብን፤በቆሎ ሳንዘራ በምንም አይነት ተአምር በቆሎ አናጭድም።በብዙ ጾም ጸሎትም ብንጮህ፤ሰው የዘራወን ብቻ ያጭድ ዘንድ ህግ ነው።መንፈሳዊነት የስንፍናና የቸልተኝነት መሸሸጊያ መሆን የለበትም።ወደ አለም ሁሉ ሂዱ፤መሄድ ማለት መንቀሳቀስ ነው፤ጸሎት ብቻ በአንድ እግር ለመሄድ እንደመሞከር ነው።እምነትና ጸሎት ያለስራ የሞተ ነው። አዎ መሄድ፤ወደ አለም ሁሉ፤የሰላምን ወንጌል፥የፍቅርን አምላክ ለሰው ዘር ማወጅ፤ማን ያውቃል? ነገ ትላልቅ መልእክተኞች ተነስተው ወደ ሊቢያ፥ሶርያ፥ኢራቅ፤ወደ አይሲሶች ሄደው የክርስቶስን ዘላለማዊ የህይወት ቃል የሚናገሩ ሊነሱ ይችላሉ።ይሄም ይቻላል። የግብጽ ክርስቲያኖች በአይሲስ ከተገደሉ በኋላ የሃገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት የክርቶስን ፍቅርና ይቅርታ ለግብጽ ህዝብና ለአለም ሁሉ አውጀዋል።በሃገራችንም የፍቅርና የይቅርታ ተምሳሌቶች፤የተጣላውን የሚያስታርቁ፤በጸሎትና በስራ የሚገለጡ ልንሆን ይገባል።የልማት አርበኞች(ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አናጺ ነበር፤ወንጌላዊ ሉቃስ ሃኪም ነበር፤ሃዋርያው ጳውሎስ ድንኳን ሰፊ ነበር)፥ የፍትህ መልእክተኞች ልንሆን ይገባል። ይሄም ይቻላል፤ሊሆን ግድ ነው።
ወገኖቻችን በአይሲስና በህገወጥ ነጋዴዎች በየመንገዱና በየቦታው ሲወድቁ ጀግነነታችን ለጠመንጃና ለጎራዴ ብቻ ነው እንዴ? አንድ ለመሆን እንጀግን፤በሃገራችን ሰላም ለማስፈን እንጀግን፤ ሃይማኖቶች፤ ብሄሮች፤ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ለመከባበርና ላለመስማማት ተስማምቶ አስቸኳዩን በአስቸኳይ ለመፍታት ለዚህ እንጀግን፤ ቤተሰብ ያለበት ቤት በእሳት ሲጋይ የእሳት አደጋ መኪናውን ማንም ይንዳው፥ ውሃውን የሚያፈሱት ማንም ይሁኑ፥ ቤቱ ውስጥ ገብቶ ህጻናቱን የሚያድነው ማንም ይሁን ዋናው መጀመርያ ሰው ይዳን፤ ከዛ ከርክራችንን ካቆምንበት እንቀጥላለን።ሰው እየሞተ አድኑን እያለ እየጮኸ “መኪናው ለምን ቀይ ሆነ?” ‘ሾፌሩን አልወደውም” ብሎ የሰውን ህይወት ለአደጋ ማጋለጥ፥ “ምስጋናውን ማን ሊወስድ ነው?” በሚል ፉክክር ውስጥ መግባት አይገባንም።”ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” አሁን ነው በትክክል የሚሰራው፤ ኢትዮጵያውያን በፍቅር፥በይቅርታ፥ለሰላም መተባበር፥መከባበር፥የድህነትን ቀንበር መስበር፤በልዩነት አንድነት፥ላለመስማማት መስማማት፤ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት አለብን፤ ነገ የኛ አይደለም፤ዛሬ ማድረግ የምንችለውን ዛሬ እናድርግ፤በነገ እንመካ።
ክርስቲያኖች ሆይ፤ ስለራሳችን መዳንና መባረክ ብቻ መጨነቁ ያብቃ፤ ሀገርን መዳን እንዳለባት ነፍስ እንያት።ሀገር ማለት ሰው ነውና።ለራሳችን ተነቃቅተንና መልእክት ከተቀበልን ብዙዎቻችን ረክተን “ጌታ እኮ ባረከኝ” ብለን ወደ ቤታችን እንሄዳለን፤ይሄ ራስ ወዳድነት ነው፤በዚህ ምድር ዋናው ያለነው ለመባረክ(ጠበቅ) ሳይሆን ለመባረክ ነው (ላላ)።ለመቀበል ሳይሆን ለመስጠት።በሚያሳፍር ደረጃ ያለውን መከፋፈልን አስወግደን በአንድነት መንፈስ ክፋትን፤ሰይጣንን፤ድህነትን፤ኢፍትሃዊነትን እንዋጋ።
ይህ የሰሞኑ መከራችን መደራረብ ቢገባን ከእግዚአብሄር ዘንድ ማስጠንቀቂያ ደወል ነው።በአይሲስ በግፍ ለተገደሉት ቤተሰቦች ድጋፍ እናድርግ፤ቤተ ክርስትያኖች ሁሉ የሞራልና የገንዘብ ድጋፍ እናድርግላቸው። በየቤተ እምነቱ ውይይት ይጀመር፤ስለሰማዩ ቤት ብቻ ሳይሆን ስለምድራዊውም ጭምር፤ ችግራችንን እንዴት እንፍታ? ልጆቻችንን ከህገወጥ አስተላላፊዎች እንዴት እንጠብቅ? ብርሃናችሁን አብሩ፤አለበለዚያ እናንተ ራሳችሁ ብርሃኑ ተወስዶባችሁ በጨለማ ትቀመጣላችሁ።ላለው(ለሰራበት) ይጨመርለታል፤ ለሌለው(ላልሰራበት) ያው ያለው ይወሰድበታል፤ እንመለስ ይሆን? ወይስ አይናችን እያየ የቀረው ሞገሳችንና ክብራችን ይወሰድብን ይሆን?
ሃይማኖቶች ሁሉ፥ በዶክትሪን ብንለያይ ሁላችንም ውስጥ “የጋራ በጎ” አለ። ሁላችንም ሰላምና ፍትህ እንፈልጋለን።በዛ ዙሪያ አብረን እንስራ።ሙስሊምና ክርስቲያን በየአካባቢው ጎረቤት አይደለ? አብሮ መንገድ አያሰራም? ሌባ ሰፈር ውስጥ ቢገባ አብሮ አያሲዝም? እሳት አደጋ ቢነሳ አብሮ አያጠፋም? ልጆቹን አንድ ትምህርት ቤት አይልክም? ባንዱ ንግድ ድርጅት አንዱ አይገለገልም? በአንድ መስሪያ ቤት አብሮ አይሰራም? ልክ እንደዛው ለሰላምና ለፍትህ አብረን እንስራ፤ ክፋትን አብረን እንዋጋ።
ለተሰዉት ቤተሰቦችና ይህን ዜና ሰምተው በአለም ዙሪያ ልባቸው ለተሰበረ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያጽናናቸው እንጸልያለን።ይሄን ጭካኔ ለፈጸሙት ደግሞ ንስሃና መመለስ እንዲሆንላቸው እንጸልያለን። እነዚህ መስዋእት የሆኑት ለእምነታቸው ነው፤ነፍሳቸው በአምላክ ፊት ነች።ጥንካሬያቸው ለኛ ትምህርት ይሁነን፤ ቃሉን ለመታዘዝ፥ ህጉን ለማክበር፥ ከመከፋፋት ወደ መቀራረብ፤ ከመጣላት ወደ መታረቅ እንድንመጣ ማንቂያ ደወል ይሁነን።
በተለያዩ መንገዶች ድምጻችንን እናሰማ፤ ለምሳሌ ብርቱካናማና ጥቁር በመልበስ ወይም ሻርፕና ሪቫን በመጠቀም በነዚህ ቀለማት ቱታ አልብሰው የጨፈጨፍዋቸውን እናስብ።
“ሁሉ ለበጎ ይለወጣል” ተብሎ እንደተጻፈ ይህ ክስተት ለክርስቲያኖችና ለኢትዮጵያውያን አንድነት የሚያመጣ፤ ይህን ተግባር ለፈጸሙት ደግሞ የመውደቂያቸው ጊዜ መቃረቡን የሚያሳይ ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ኢትዮጵያም እግዚአብሔርን ትባርክ(ትታዘዝ፥ታመስግን፥ታገልግል)
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ
ዋሽንግተን ዲሲ

Advertisements