Our Prayer was for Unity and Reconciliation.

ምርጫ ቦርድ አንድነትን ለእነ ትግስቱ አወሉ፣ እንዲሁም መኢአድን ለእነ አበባው መሃሪ መስጠቱን ዛሬ ጥር 21/2007 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳወቀ፡፡
ምርጫ ቦርድ በመግለጫው ‹‹ምርጫ የሚገባ ፓርቲ በማስፈለጉ፣ ‹‹የእነ በላይ ቡድን ፓርቲውን የሚያስቀጥለው ባለመሆኑና ፓርቲውን እንደ ፓርቲ እንዲቆይ ስለሚፈለግ ዛሬ ጥር 21 ቦርዱ ባደረው አስቸኳይ ስብሰባ እነ ትግስቱ አወሉ ወደ ምርጫ እንዲገቡ ወስኗል›› ብሏል፡፡
‹‹ሁለቱም ችግር አለባቸው፡፡ እኛ ያየነው በአንጻራዊነት ነው፡፡ የእነ ትግስቱ አወሉ ቡድን ችግር ቢኖርበትም ከዛኛው የተሻለ ነው፡፡ እውቅናውን የሰጠነው ለቦርዱ ለሚታዘዘው ነው፡፡›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አንድነት የተሰጣቸው የእነ ትግስቱ ቡድን፣ እንዲሁም መኢአድ የተሰጣቸው የእነ አበባው መሃሪ ቡድን በአሁኑ ወቅት ሁለቱንም ፓርቲዎች ወክሎ ጽ/ቤት ከሚገኘው የፓርቲ አመራር ጋር አለመግባባት በመፍጠራቸው በውጭ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

UDJ,Meiad
አቶ አበባው (በስተግራ) ፣ አቶ ትእግስቱ (በስተቀኝ)

Advertisements

ማርቲን ሉተር ኪንግ፥ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴና ኢትዮጵያ

“ማርቲን ሉተር ኪንግ ለአሜሪካ የተላከ ነቢይ ነው” ቢሊ ግራሃም (ታዋቂው አሜሪካዊ ወንጌላዊ)
“ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት የቢሊ ግራሃም የንስሃ መልእክትና የማርቲን ሉተር ኪንግ የፍትህ መልእክት ናቸው፤አንዱ ያለአንዱ አይሄድም።” ሬቨረንድ ሳሙኤል ሮድሪጌዝ (የአሴምብሊዝ ኦፍ ጋድ ፓስተርና የአሜሪካ ሂስፓኒክ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚደንት)
ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ የነጻነት ትግል ምሳሌነት የተማረከ ነበር፤
ሁለቱ በተገናኙበት ጊዜ ማርቲን ሉተር ኪንግ “ዓይኖቼ ይሄን ክብር አይተዋል፥እግዚአብሔር ይመስገን ነጻ ህዝቦች ነን” ብሏል።ንጉሱም አሜሪካን በመጡበት በ1967 የፓስተሩን መካነ መቃብር ጎብኝተዋል።
በስሙ ብሄራዊ በዓል የተሰየመለት ብቸኛው አሜሪካዊ ማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን ዛሬ ታስቧል።
ይህ ታላቅ ሰው በጥቁሮች ላይ ይካሄድ የነበረውን የዘር መድልዎ እንዲቆም ዋናውን ሚና የተጫወተ የቤተ ክርስቲያን ፓስተር ነው።
ማርቲን በፍትህና በሰላም ዙሪያ ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋ ትልቅ እንደሆነና ይህንንም ካልተወጣች ከዕድር ተለይታ እንደማትታይ በአፅንኦት ተናግሯል።
“ቤተ ክርስቲያን የመንግስት ጌታም ሆነ አገልጋይ ሳትሆን ህሊናው ናት” የሚል አስደናቂ መልዕክት አስተላልፏል።
ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሰረተው ሰማያዊ ትምህርት እንድታስተምርና ድሆች እንድትረዳ ብቻ ሳይሆን ዕርቅ፥ሰላምና ፍትህን በማስፈኑ ሂደት የመሪነት ሚና እንድትጫወት ጭምር ነው።
ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲናገር “ቤተ ክርስቲያን ለፍትህና ለሰላም ድምጿን ካላሰማች የሚሊዮኖችን ከበሬታና እምነት ታጣለች፤ይልቁንም ከተሳሰረችበትና ከሚገድላት status quo ወይም “ባለህበት እርጋ፥ተስማምተህ በሰላም አርፈህ ኑር” አስተሳሰብ ወጥታ የሰዎችን መንፈስ ለተቀደሰ የፍቅር የሰላምና የፍትህ ዓላማ የሚያነሳሳ ታሪካዊና ትንቢታዊ ሃላፊነቷን መወጣት አለባት”ብሏል “ያን ጊዜ የሰው ልጆች ቤተ ክርስቲያን በጨለማ ላሉ ብርሃን መሆኗን ይረዳሉ” በማለት ሬቨረንድ ኪንግ ታላቅ ምክሩን ለግሷል።
የዚህን ሰው ታሪክ ስናስብ ለሃገራችን ቤተክርስቲያን ምን ትምህርት ትቶልናል የሚለውን በመጠየቅ እኛም በተራችን የእርሱን ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያ ሰላምና ፍትህ የሰፈነባት ሃገር እንድትሆን ድርሻችንን እንወጣ፤የሰላምና ፍትህ አጀንዳ ደግሞ የአንድ ቄስ ወይም ክርስቲያኖች ብቻ ጉዳይ ስላልሆነ በሁሉም ሃይማኖትና ብሔር ያለን ኢትዮጵያውያን ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ በአንድነት እንነሳ።
በመጨረሻም ማርቲን ሉተር ኪንግ ለጥቁሮች መብት እየተከራከረ ከነጮቹ መንግስት ጋር የበሰለ ድርድር በማድረግ መንግስት የዕኩልነት ህግ እንዲያወጣ አስደርጓል።ከውይይት፥ድርድርና መግባባት ይልቅ ጥላቻ፥ በቀልና የበላይነት ስሜት ለገነነበት የሀገራችን ሁኔታ ታላቅ ትምህርት ይተውልናል።
“ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ።ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”ሮሜ ምዕ12
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ

ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ

የኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ዓላማ “የሚያስተራርቁ ብጹአን ናቸው” እንዲሁም “መልካሙን ስራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ” ተብሎ እንደተጻፈ እንደ ክርስቲያንነታችን የሃገራችን ብርሃንና የወንጌል ህያው ምስክር መሆን ስለሚጠበቅብን ያን ድርሻችንን ለመወጣት የሚንቀሳቀስ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው።አገልግሎቱ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ የሌለው ከማንኛውም የፖለቲካና የቤተ እምነት ድርጅቶች ያልወገነ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅር አብሮ የሚሰራ ነው። ማየት የምንፈልገው ሃገራችን ውስጥ ዕርቅ ሰላም ፍትህና ብልጽግና ሲሰፍን ነው።
ethiopiariseandshine.wordpress.com

ፎቶዎች; ቀሃስ በፓስተሩ መካነ መቃብር የአበባ ጉንጉን ሲያኖሩ፥ሬቨረንድ ማርቲን ሉተር ኪንግና ወንጌላዊ ቢሊ ግራሃም
mlk-hsmlk- hselassie -mlkbilly-martin

ፍትህና ሰላም በምርጫ 2007!

Girma HMD - 1የአንድነት ፓርቲ ም/ፕሬዚደንትና የተወካዮች ምክር ቤት አባል የተከበሩ ግርማ ሰይፉ ከ ጠ/ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጋር

ክርስቲያኖች ለሀገር መሪዎችና ለሰላም እንድንጸልይ ታዘናል።እርቅን፥መግባባትን ማወጅ ሃላፊነታችን ነው፤የሚያስተራርቁ ብጹአን ናቸው ተብሎ ተጽፏልና።
በቅርቡ በሀገራችን ምርጫ ይካሄዳል።ከዚሁ ጋር ተያይዞ ፉክክር፥ክርክር፥ውድድር ይኖራሉ።አንዳንዴም በሌላውም ዓለም እንደሚታየው መረር ያሉና መስመር ሊያስለቅቁ የሚችሉ ሽኩቻ ስድብና በጥላቻ ላይ የተመሰረታ ዘመቻ ይታያል።ከዚህም በፊት በሀገራችን ብዙ ሰዎች የሞቱበት አሳዛኝ ሁኔታ ተከስቶ ነበር።ያ እንዲደገም አንፈልግም።
ለሰላምና ለመግባባት እንጸልያለን።
ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ውድድር ማድረግ እንዲችሉ ሜዳውን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ማመቻቸት ይጠበቅበታል። ምርጫ ቦርድ፥ፍርድ ቤትና ሚዲያው ሁሉንም እኩል የሚያስተናግዱ ሊሆን ይገባል።ኢትዮጵያ የምታድገው የተለያዩ ሃሳቦች ተፋጭተው ከውድድር በሚገኝ የነጠረ አስተሳሰብ ነው።ተቃዋሚ ሲኖር ለገዢው ፓርቲ መስተዋት ይሆናሉ፤ቁጥጥርና ክትትል ያደርጋሉ፤ሙስናን ሌሎች ህገወጥነትን ያጋልጣሉ።ተወዳድረው ከተመረጡ ደግሞ ሀገር የመምራት እድል ያገኛሉ።
የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች እንግልትና እስራት በተለያዩ ባለስልጣኖች ይደርስባቸዋል።እነዚህ በአግባቡ ታይተው መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል።ወንጀል የሰሩና ያልሰሩ መለየት አለባቸው።ባልተጣራ ሁኔታና በግል ቂም በቀል ንጹህ ሰው በፍጹም መንገላታት የለበትም።

መንግስት ምንም አላደረገም ማለት አይቻልም።ሀገሪቷ ከቀደሙት መንግስታት የተሻለ የዲሞክራሲ ብልጭታ ታይቶባታል።ሆኖም ግን ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት በባለስልጣኖች ይፈጸማል። ሳይውል ሳያድር በዜጎች ላይ በደል የሚያደርሱት ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።የሰብአዊ መብት ጥሰት ከባድ ወንጀልና ሃጢያትም ነውና።
ሰሞኑን በአንዳንድ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል ያለው መቃቃር በሰላምና በመግባባት እንዲያልቅ እንጸልያለን።
እነዚህ ፓርቲዎች ክፍተኛ ዝግጅት አድርገው ለመወዳደር ተነስተዋል፤አንዳንድ ግድፈቶች አሉ ከተባለ በማለፍ በተቻለ መጠን ምርጫውን እንዲካፈሉ መንግስት መጣር አለበት።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመካከላቸው የሚነሱትን ልዩነቶች ብስለት በተሞላበት መንገድ በውይይት መፍታትና አንድነት መፍጠር ሀገራዊ ግዴታቸው መሆኑን በውሉ ሊያጤኑት ይገባል።
በአንዳንዶች የምናየው ስር የሰደደ ጥላቻ፥ስድብ፥የሰውን ስብእና ማዋረድና ዘረኝነት መግባባትንና እርቅን ይጎዳልና በአስቸኳይ መቆም አለበት።
በሀገራችን የዲሞክራሲ ግንባታ ትልቅ ሚና የሚጫወቱና ባሁን ሰአት ካሉት ፓርቲዎች ሁሉ በተሻለ ደረጃ ላይ ካሉት ከአንድነትና መኢአድ ጋር ያለው ችግር ተወግዶ ወደ ምርጫው እንዲገቡ ያስፈልጋል።ምርጫ ቦርድም ነገሩን በቅንነት በማየት ጥቃቅን ግድፈቶችን ቸል በማለት ወደ ምርጫው እንዲገቡ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ብለን እናምናለን።ይህ ካልሆነ ግን ለሚገነባው የመድብለ ፓርቲ( multi-party) ሲስተምና ለሃገሪቷም ውድቀት ይሆናል።እነዚህም ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግል ላይ ተስፋ ይቆርጣሉ።እነርሱ ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነት(Civil Disobedience) እንገባለን እያሉ ነው፤በዚህም ሀገሪቷ ወደ አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ የምትገባ ሲሆን ይህ ደግሞ የሚካሄዱትን የልማት ስራዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊያዳክም ይችላል።
ዛሬ በኢትዮጵያ አንዱ የጎደለው ነገር ቅንነት ነው።ቅንነት ከሌለ መጨቃጨቅ፥መካሰስ፥ፍርድ ቤት መንከራተት ብቻ ይሆናል።አንዱ አንዱን ለማጥቃት ሰበብና ምክንያት ብቻ ነው የሚፈልገው፤አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱትም አይነሳምና።
ስለሆነም ችግሮች ሁሉ የሚፈቱት በመነጋገርና በመከባበር ነው።ያለፈውን በደል ይቅርታ በመጠያየቅ ህዝባችን ከድህነት የሚወጣበትን መንገድ ማፋጠን እንጂ እኛ ለስማችንና ለክብራችን ስንከራከር ህዝብ ማለቅ የለበትም።
እግዚአብሔርም ይሄን አይወድም፤ይቅር ተባባሉ፥ተከባበሩ፥ክፉን በመልካም አሸንፉ እንጂ በክፉ አትሸነፉ ነው ያለው።ሌላ አማራጭ የለም።
“እርስ በርስ መግባባት፥ሀገርን መገንባት” መርሃችን ይሁን።
አብያተ ክርስቲያናትና የሃይማኖት ተቋማት እውነትን በፍቅር የመናገር ሃላፊነትና ግዴታ አለባቸው።
ቅንነት ለኢትዮጵያ!
ፍቅርና ፍትህ ለኢትዮጵያ!
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ