“በኢትዮጵያ በተለያዩ ቡድኖችና ሃይሎች መካከል ሰላምና መግባባት እንዴት ይመጣል?”

“በኢትዮጵያ በተለያዩ ቡድኖችና ሃይሎች መካከል ሰላምና መግባባት እንዴት ይመጣል?”
የ “Ethiopia This Week” ሬድዮ ቃለ መጠይቅ ለወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው
online:  https://ia902607.us.archive.org/24/items/October122014P/October122014p.mp3

Advertisements

“ሁሉ በአገባብና በስርዓት ይሁን”

የኤምባሲው ክስተትና የማክሰኞው ሰልፍ

በጥንታዊቷ የቆሮንቶስ ከተማ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ተአምራዊ የጸጋ ስጦታ ይጠቀሙ ነበር።በሽተኞች ይፈወሳሉ፥መገለጦች ይነገራሉ።ከዚህ ጋር ግን አብሮ ችግሮች ነበሩ።ይሄ ሁሉ ሲሆን እነዚህ ወገኖች እርስ በርስ ይከፋፈሉ ነበር፥አይደማመጡም፥ ባጠቃላይ የፍቅር ማነስ፥የልጅነት ጸባዮች፥ የራሳቸውን ክብር ማስቀደምና ለሁሉ የማይጠቅም ነገሮች ማድረግ ጎልተው ይታዩ ነበር።ለዚህም ነው ሃዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር የሰላም አምላክ እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” እንዲሁም “በልሳኖች ከመናገር አትከልከሉ ሁሉ ግን በአገባብና በስርአት ይሁን” ያለው።

ሰሞኑን በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ ኤምባሲ የተከሰተው ሁኔታ እጅግ አሳዛኝና “ወዴት እየሄድን ነው?” ብሎ የሚያስጠይቅ ነው።
የሰብአዊ መብት ጥያቄ አለን በሚሉና በኤምባሲው መካከል በተፈጠረው ግጭት ጥይቶች ተተኩሰዋል፤የሰዎች ህይወት አደጋ ላይ ወድቋል።የዓለም የዜና አውታሮች ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ዘግበውታል።ግን በበጎ ሳይሆን ‘ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተጋጩ” በሚል ነዉ።
ነጻነት፤ፍትህ፤እኩልነት፤ሰብአዊ መብት እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ የሰጠው ማንም ሊከለክለን የማይችል መለኮታዊና የተፈጥሮ ስጦታ ነው። እነዚህን መብቶች መጠየቅ አግባብ ነው፤ የሚመለከተውም ክፍል ጥያቄዎችን ማስተናገድና መልስ መስጠት ግዴታው ነው።የሰብአዊ መብት ረገጣ ከባድ መንፈሳዊ ሃጢአትና ምድራዊ ወንጀል ነው። ከዚህ አንጻር የሚመለከተው የመንግስት አካል ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሁኔታውን ከጠያቂው አካል ጋር መወያየትና የተፈጸሙ በደሎች ካሉ ማስተካከል ግዴታው ነው።
ይሄ ሁሉ ግን መሆን ያለበት ከላይ እንዳየነው ያለ ሁከት በአገባብና በስርአት ነው። ጠያቂው አካል ያለ ምንም ድብቅ ተልእኮና ሁከት ጥያቄውን ማቅረብ አለበት።ሌላ የፖለቲካና የስልጣን አጀንዳ ካለን በግልጽ መነጋገር እንጂ ከሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ጋር እንዳይደባለቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።”እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” ተብሎ እንደተጻፈ አቀራረቡ በአክብሮት ላይ የተመሰረተ ካልሆነ ይልቁንም በስድብና በማዋረድ በስርአተ አልበኝነት ከሆነ ተጠያቂውም የመመለስ ሃላፊነት አይኖረውም።ስሜትና ንዴት ቢኖርም ከህግ ውጭ መሆን መልሶ የሚጎዳው የተነሱበትን ዓላማ ነውና ጥንቃቄ ያሻል።ተያይዞ ገደል መግባት ነው።ይህ ደግሞ ለሃገራችንም ለምንሟገትላቸው ሰዎችም አይጠቅምም።
ስለሆነም ኢትዮጵያውያን እንረጋጋ፥ገና የምግብና መድሃኒት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በየቀኑ ለሞት እደጋ የተጋለጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን አሉ።ክርስቶስ እንዳለው “ተርቤ አላበላችሁኝም፥ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፥ታርዤ አላለበሳችሁኘም፥ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝም”።እግዚአብሔርም ስለሚጠይቀን ህዝባችንም ስለሚጠብቀን በነገር ሁሉ ሚዛን እንጠብቅ።
ሰላማዊነትና ህጎችን ማክበር ከዜጎች የሚጠበቅ ሲሆን ህዝብን በሙላት ማሳተፍ፥ታጋሽ የአባትነት መንፈስ ከመንግስት ይጠበቃል።

ማሳሰቢያ
ነገ ማክሰኞ oct 7,2014 ሁለት የተለያዩ ቡድኖች በተመሳሳይ ሰዓት በስቴት ዲፓርትመንት ሰልፍ ጠርተዋል። ሁሉም ወገን ሃሳቡን በህጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይጠበቅበታል። የሁለቱም ቡድን ዓላማ ለአሜሪካ መንግስት መልእክት ማስተላለፍ ነውና ከዓላማቸው ሳይወጡ ሰልፉን እንዲያካሂዱ ማሳሰቢያችንን ከአደራ ጋር እናስተላልፋለን። በተመሳሳይ ቦታና ጊዜ ስለሚካሄድ በሁለቱም ወገን መተነካኮስና መሰዳደብ እንዳይኖር ሁሉም ራሱን በመግዛት የመጣበትን ዓላማ ብቻ እንዲያስፈጽም ያስፈልጋል።ይህን አለማድረግ ከተነሱበት ፕሮግራም ውጭ ከማውጣቱም በላይ በህግም ከባድ መዘዝ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል።በአሜሪካ ህግን በተመለከተ ቀልድ እንደሌለና የዕለት ተዕለት ኑሯችንና ቤተሰባችንን ሊጎዳ የሚችል ድርጊት እንዳይፈጸም ታላቅ ጥንቃቄ ያሻል።በቅዱስ መጽሃፍ እንደተጻፈ አንዱ የሚሰጠን ጸጋ ራስን መግዛት ነው፤ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን “ቢቻላሁ በናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” ይላል።ከሰዎች ጋር በሃሳብ ለመለያየት መጣላት መሳደብ አያስፈልግም፤በሰላም እየኖርን፥በሰላማዊ መንገድ እየተጠቀምን አጀንዳችንን ማስፈጸም እንችላለን።ላለመስማማት ተስማምተን፤አለመስማማትን እንደ ውበት መውሰድ የይገባናል።ዝሆንንና ትንኝን የፈጠረ አምላክ በልዩነት ያምናል።
“አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን ዓመል ያጠፋል፤ ሰው የዘራውን ያንኑ ያጭዳልና በስጋ የሚዘራ (ጠብ፥ዓመጽ፥ስድብ፥ቁጣ) ሞትን ያጭዳል በመንፈስ የሚዘራ (ትዕግስት ይቅርታ ብልህነት አክብሮት ራስን መግዛት) የዘላለምን ህይወት ያጭዳል።”
ኢትዮጵያውያን እጆቻችንን ወደ እግዚአብሔር እንዘርጋ እንጂ ለስሜታችን አንገዛ።የዓለም ሚዲያ መተረቻ በመሆን የፈጣሪያችንን ስም እንዳናሰድብ እርሱ ይርዳን፥አሜን።
“ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም..ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት…ምቀኝነት፥ መግደል። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።”
“ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን።ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ… የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ … የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና።ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና።ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።”ከሮሜና ገላትያ መልእክቶች የተወሰደ

ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ