ማርቲን ሉተር ኪንግ፥ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ሁኔታ

 ሰሞኑን የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን ታስቧል ።ይህ ታላቅ ሰው በጥቁሮች ላይ ይካሄድ የነበረውን የዘር መድልዎ እንዲቆም ዋናውን ሚና የተጫወተ የቤተ ክርስቲያን ፓስተር ነው።ማርቲን በፍትህና በሰላም ዙሪያ ቤተ ክርስቲያን ድርሻዋ ትልቅ እንደሆነና ይህንንም ካልተወጣች ከዕድር ተለይታ እንደማትታይ በአፅንኦት ተናግሯል።

“ቤተ ክርስቲያን የመንግስት ጌታም ሆነ አገልጋይ ሳትሆን ህሊናው ናት” የሚል አስደናቂ መልዕክት አስተላልፏል።

በታሪክ ብዙ እንደምንረዳው ይህ የተከሰተ ጉዳይ ነው።ያ ደግሞ መንግስትን ብቻ ሳይሆን እራሷን ቤተ ክርስቲያንን ጎድቷታል።የጣልያን ቤተ ክርስቲያን የሙሶሎኒ አገልጋይ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ የተደረገውን የግፍ ወረራ ከመቃወም ይልቅ ዝምታን እንዲያውም መደገፍን መርጣለች።

ክሩሴደርስ በተባለው ጦርነት በወቅቱ እጅግ ሃያል የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ከወንጌል ትምህርት ውጭ በሌሎች ሃይማኖቶች ላይ ወረራ ለማካሄድ የመንግስትን ጦር ሃይል በመጠቀም በሰው ልጅ ታሪክ የማይረሳ ጥቁር ነጥብ ጥላ አልፋለች።

ናዚዎችም አይሁዶችን በግፍ ሲጨፈጭፉ ቤተ ክርስቲያን ዝምታን መርጣለች።ምናልባት ድምፅዋን አውጥታ ብትቃወም ኖሮ  ሚሊዮን አይሁዶችን ከመሞት ታድን ነበር የሚሉ ታሪክ ፀሃፊዎች አሉ።በርግጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሮማው ዳግማዊ ዮሃንስ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል።ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ቢሆንም ቢያንስ የሚቀጥለው ትውልድ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሰራ ይረዳል።ለሞቱት ቤተሰብም ከምንም ይሻላል የሚያስብል ነው።

ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የመሰረተው የሃይማኖት ትምህርት እንድታስተምርና ድሆች እንድትረዳ ብቻ ሳይሆን ዕርቅ፥ሰላምና ፍትህን በማስፈኑ ሂደት የመሪነት ሚና እንድትጫወት ጭምር ነው።ዋናው ጥያቄ ከእንግዲህ ወዲህ ምን እናድርግ ነው።ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲናገር ቤተ”ክርስቲያን ለፍትህና ለሰላም ድምጿን ካላሰማች የሚሊዮኖችን ከበሬታና እምነት ታጣለች፤ይልቁንም ከተሳሰረችበትና ከሚገድላት status quo ወይም “ባለህበት እርጋ፥ተስማምተህ በሰላም አርፈህ ኑር” አስተሳሰብ ወጥታ የሰዎችን መንፈስ ለተቀደሰ የፍቅር የሰላምና የፍትህ ዓላማ የሚያነሳሳ ታሪካዊና ትንቢታዊ ሃላፊነቷን መወጣት አለባት”ብሏል “ያን ጊዜ የሰው ልጆች ቤተ ክርስቲያን በጨለማ ላሉ ብርሃን መሆኗን ይረዳሉ” በማለት ሬቨረንድ ኪንግ ታላቅ ምክሩን ለግሷል።የዚህን ሰው ታሪክ ስናስብ ለሃገራችን ቤተክርስቲያን ምን ትምህርት ትቶልናል የሚለውን በመገንዘብ እኛም በተራችን የርሱን ፈለግ በመከተል ኢትዮጵያ ሰላምና ፍትህ የሰፈነባት ሃገር እንድትሆን ድርሻችንን እንወጣ፤የሰላምና ፍትህ አጀንዳ ደግሞ የአንድ ቄስ ወይም ክርስቲያኖች ብቻ ጉዳይ ስላልሆነ በሁሉም ሃይማኖትና ብሄር ያለን ኢትዮጵያውያን ለዚህ የተቀደሰ ዓላማ በአንድነት እንነሳ።
በመጨረሻም ማርቲን ሉተር ኪንግ ለጥቁሮች መብት እየተከራከረ ከነጮቹ መንግስት ጋር የበሰለ ድርድር በማድረግ መንግስት የዕኩልነት ህግ እንዲያወጣ አስደርጓል።ከውይይት፥ድርድርና መግባባት ይልቅ ጥላቻ፥በቀልና የበላይነት ስሜት ለገነነበት የሀገራችን ሁኔታ ታላቅ ትምህርት ትቶልናል።     

   “ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ።ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”ሮሜ ምዕ12 እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ፤

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ፤አሜን።

ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ

የኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ዓላማ “የሚያስተራርቁ ብጹአን ናቸው” እንዲሁም “መልካሙን ስራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ” ተብሎ እንደተጻፈ እንደ ክርስቲያንነታችን የሃገራችን ብርሃንና የወንጌል ህያው ምስክር መሆን ስለሚጠበቅብን ያን ድርሻችንን ለመወጣት የሚንቀሳቀስ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው።አገልግሎቱ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ የሌለው ከማንኛውም የፖለቲካና የቤተ እምነት ድርጅቶች ያልወገነ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅር አብሮ የሚሰራ ነው። ማየት የምንፈልገው ሃገራችን ውስጥ ዕርቅ ሰላም ፍትህና ብልጽግና ሲሰፍን ነው።

Advertisements

ፍቅር ወይስ ፍትህ? (ክፍል 1)

“ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ “

ሰሞኑን የጌታን ልደት አክብረናል፤ከጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምና ከዮሴፍ የምንማረውን ጠቃሚ ትምህርት በ 2 ክፍል በእግዚአብሔር ስም አቀርባለሁ

ዮሴፍ ማርያም ከርሱ እንዳልፀነሰች ሲያውቅ ሁለት ነገር ለማድረግ ወስኖ ነበር።በኋላ ገብርኤል ማርያም የፀነሰችው ከመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ሲያውቅ ውሳኔውን መቀየሩ ይታወቃል።ከዚያ በፊት ግን በወቅቱ በነበረው ውስን መረጃ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር የወሰነው።

መጀመሪያ የወሰነው ሊተዋት ነበር።አንዲት ሴት ለባልዋ ወይም ለእጮኛዋ ታማኝ ካልሆነች ወንዱ ሊለያት መብቱ ነው፤ፍትህ ነው፤ታማኝ ካልሆነች ሴት ጋር ለመኖር ማንም ሊያስገድደው አይችልም።

ዮሴፍ ግን መብቱንና ፍትህን ሊያስጠብቅ ቢወስንም ግን ክፉና ደንታ ቢስ ሰው አልነበረም።ነጻነቱን የሚያስከብረው የሌላን ሰው ስም በማጥፋትና በጥሎ ማለፍ አስተሳሰብ አልነበረም፤ይልቁንም  ወንጌል “ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ” ነው  የሚለው(ማቴ 1:19)።ይህ ርህራሄን፥አርቆ አሳቢነትን፥ፍቅርን ያሳያል።ስም ማጥፋት፤ክብርን ማዋረድ፥የሃገር መሳቂያ ማድረግ ይችል ነበር፤የመረጠው መንገድ ግን መብቱን አስከብሮ ፍትህን ማስፈንና በፍቅር መንገድ በሰላማዊ መንገድ ለጉዳዩ እልባት መስጠት ነው።

ዛሬም እኛ ሁለቱን ማለትም ፍቅርንና ፍትህን ሚዛናዊ አድርገን መጓዝ ይጠበቅብናል።አንዳንዶች ፍቅር ፍቅር ሲሉ ፍትህን ቸል ያሉ አሉ፤የሰዎች መብትና ነጻነት ሲነካ ፥ አድልዎ እያዩ ” መጸለይና መውደድ ይበቃል” ይላሉ።ይህ ስህተት ነው።ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ መቅደስ ያየውን የለዋጮችንና ሻጮችን ንግድ አውግዟል እንጂ አላመቻመቸም።ስለዚህ ፍቅር አስፈላጊ ነው ግን አይበቃም።

ሌሎች ደግሞ ፍትህ ፍትህ ይላሉ በደረቁ፤የሚስብ፥ጠላትን ወዳጅ የሚያደርግ ስብእና የላቸውም።የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ዓይነት።ዱቄቱ የትም ከተፈጨ መዘዝ አለው፥ዕድሜም አይኖረውም።መሬት እንኳን ከመታረሱ በፊት መቆፈርና ውሃ መጠጣት አለበት፤ከዚያ በኋላ የተፈለገውን ውጤት ይሰጣል።ባል ከሚስቱ ጥሩ ምላሽ ለማግኘት ፍቅርንና ልስላሴን ማሳየት ይጠበቅበታል።ያን ጊዜ ሚስት ያልጠበቀውን አስደናቂ ፍቅር ትመግበዋለች።ለዚህ ነው ክርስቶስ ሲናገር እግዚአብሔርን ለማምለክ እውነትና መንፈስ ያስፈልጋል ያለው።እውነት ኖሮን የሚያለሰልሰውና የሚያጣፍጠው መንፈስ ከሌለን ደረቅ እውነት ለማንም አይዋጥም።ይህ ማለት ጠንካራ አንሁን አቋም አይኑረን  ማለት አይደለም፤ ሃሳባችንንና ዓላማችንን ሌሎች እንዲቀበሉት የሰለጠነ የማሳመንና የመደማመጥ ባህል ይኑረን ለማለት ነው።ስናዳምጥ እንደመጣለንና!

ስለሆነም ለዕርቅ፥ለሰላም፥ለውይይትና ለይቅርታ ልብ ይኑረን።እንዲህ ከሆነ ሃገራችንን ማንም አይከፋፍላትም፥የውጭ ጣልቃ ገብነትም አያሰጋንም።ሰላምና ልማት የተረጋገጠ ይሆናል።እንገናኝ፥እንወያይ፥ተቃራኒ ሃሳብ ለመስማት እንዘጋጅ፤ለኢትዮጵያ የምናስብ እኛ ብቻ እይደለንም፤በኛ ሃሳብ የማይስማማውን ጠላት አድርጎ ከመፈረጅ እንቆጠብ፤በልዩነት አንድነት መስርተን አብረን መስራት እንችላለን።ዝሆንና ትንኝን የፈጠረ አምላክ በልዩነት ያምናል።”አንድነት” እንጂ “አንድ ዓይነት” መሆን የለብንም።

ዮሴፍ ማርያም ከመንፈስ ቅዱስ እንደፀነሰች ካወቀ በኋላ ተቀበላት፤ከዛ ደግሞ የምንማረውን ትምህርት “መግባባትና መገንባት” በሚለው ርዕስ በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ።

ፍትህና  ፍቅር ለኢትዮጵያ! እግዚአብሔርን ሀገራችንን ይባርክ።

 ዳንኤል ጣሰው

ከ ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ!

የ ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ዓላማ “የሚያስተራርቁ ብጹአን ናቸው” እንዲሁም “መልካሙን ስራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ” ተብሎ እንደተጻፈ እንደ ክርስቲያንነታችን የሃገራችን ብርሃንና የወንጌል ህያው ምስክር መሆን ስለሚጠበቅብን ያን ድርሻችንን ለመወጣት የሚንቀሳቀስ መንፈሳዊ አገልግሎት ነው።አገልግሎቱ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አጀንዳ የሌለው ከማንኛውም የፖለቲካና የቤተ እምነት ድርጅቶች ያልወገነ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጋር በፍቅር አብሮ የሚሰራ ነው። ማየት የምንፈልገው ሃገራችን ውስጥ ዕርቅ ሰላም ፍትህና ብልጽግና ሲሰፍን ነው።

አሁንም እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!