መልዕክተ መለኮት ለኢትዮጵያውያን በ2006

መልዕክተ መለኮት ለኢትዮጵያውያን በ2006
eth rise
 
ለኦርቶዶክስ፤ሙስሊም፤ወንጌላውያን፤ካቶሊክ፤ለኢትዮጵያ መንግስትና ተቃዋሚ ኢትዮጵያውያን  ወገኖች በሙሉ
በአዲስ ዓመት አዲስ አስተሳሰብ
ይህን መልእክት ለእነእገሌ ነው ከማለት የኔ መልእክት ነው ብላችሁ እንድትወስዱት በትህትና እለምናችኋለሁ።
የሰው ልጅ ህይወት አንዱ መገለጫ ማደግ፤መለወጥ፤መብሰል፤የበለጠ ዕውቀት መገብየት፤ከይሉኝታና ፍርሃት ነጻ መሆን ይገኙበታል።አስተሳሰባችን የተሳሳተም ከሆነ ወይም ከተጠራጠርን አላውቅም፤ተሳሰቼ ነበር፤ስለጉዳዩ የበለጠ ማጥናት አለብኝ በማለት በትህትና አቋማችንን ማስተካክል ይጠበቅብናል።ከእንግዲህ ወዲህ ለሰው ብለን ወይም ለቲፎዞ ወይም ለጥቃቅን ጥቅሞች ከህሊናችን ድምጽ መራቅ የለብንም።የሰው ህሊና የእግዚአብሔር  መብራት ነውና።
ለሰው ልጆች ሰላምና ጤና መርዝ ከሆኑት መካከል ጥላቻ አንዱ ነው።ዱሮ፤ትናንት በድሎኛል፤ቂም ይዤአለሁ፤እበቀላለሁ  የሚሉ ሃሳቦች በይቅርታ መወገድ አለባቸው፤አለበለዚያ እኛንና አገራችንን ያጠፋሉ።ያለ ይቅርታ ኑሮ የለም፤ጤና የለም፤ተስፋ የለም፤ህይወት የለም፤አገር የለም፤ሊኖር አይችልም፤በሚቀጥለውም ዓለም ተስፋ የለውም።እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ካላላችሁ የሰማይ አባታችሁም ይቅር አይላችሁም።
ይህ ሲባል ሰው እንደፈለገ ይበድለን ማለት አይደለም።ነገር ግን ቀርቦ በሰላማዊ መንገድ እርስ በርስ በመነጋገርና አብሮ በሰላም ለመኖር በመወሰን፤ችግሮችም ሲፈጠሩ በትዕግስት አንዱ የአንዱን ሃሳብ በመረዳት መፍትሔ በመፈለግ ለልጆቻችን ሰላማዊትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስተላለፍ እንችላለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፤ከሰማይ ምድር መፈጠር ጋር ስምዋ በዘፍጥረት መጽሐፍ ከማንም ሀገር በፊት የተጻፈ፤የሙሴን ጽላት እስከዛሬ ያስቀመጠች፤የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን በማምለክ ከእስራኤል ቀጥሎ በዓለም የመጀመሪያዋ ታሪካዊትና ጥንታዊት ሀገር ነች።ስልጣኔዋ በዓለም ከመግነኑ የተነሳ የግብጽ ፈርኦኖች ስልጣኔ ከኛ የተቀዳ እንደሆነ ታሪክ ይመሰክራል።  ለነጮች ወረራ ያልተገዛች፤ ብቸኛዋ የጥቁር ሃገር ከመሆንዋም በላይ እንዲያውም እንደ ዳዊትና ጎልያድ በህዝቦችዋ እምነትና አንድነት እንዲሁም በእግዚአብሔር ተዓምራዊ ሃይል ዘመናዊውን የነጭ ጦር ሃይል አሸንፋ ነጻነትዋን ያስጠበቀች ኩሩ የአፍሪካ መመኪያ ነች።
ይህ ሆኖ ሳለ ከጥንታዊነታችን ጋር አብረው የቆዩ ጥንታዊ ችግሮችና አዳዲስ ተግዳሮቶችም አሉ።
 ሀገራችን  ከዚህ ሁሉ ታላላቅ እውነታዎች ጎን ለጎን አሁን ያለችበት ሁኔታ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው።በተለይ ካለፉት አርባ ዓመታት ወዲህ ጦርነት ረሃብና የርስ በርስ ግጭት መለያችን ሆኖ ቆይቷል።በዚህ ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለሞት ለበሽታና ለስደት ተጋልጠዋል።ስማችን በዓለም ዙርያ ተዋርዶ አንገታችንን እንድንደፋ አስገድዶናል።”የሟቹን ሞት አልፈቅድም”ያለው ፈጣሪያችን “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ብሎ ቃል ገብቶልናል።ይህ ተስፋ ሀገራችን የአይሁድንና የክርስትና ሃይማኖት ስትቀበል ተፈጽሟል ብለው የሚያምኑ ቢኖሩም ቃሉ ዘላለማዊ ነውና ዛሬም ይሰራል።ከእንግዲህ ወዲህ በሃገራችን ጦርነት፤ረሃብ፤በሽታና የርስ በርስ ግጭት አንሻም።
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ባሁን ሰዓት ሀገራችን በዲሞክራሲና በልማት ጎዳና እየገሰገሰች ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ህዝቡ እየደኸየ ነው፤ሰብአዊ መብት እየተረገጠ ነው ይላሉ።በዚህም ሆነ በዚያም ግን ብዙ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ማንም እውነተኛ ሰው አይክደውም።በዘር፤በሃይማኖትና በቋንቋ ሳንከፋፈል የየራሳችንን ሃይማኖትና ቋንቋ እያስፋፋን፤እያጠናከርን ተከባብረን፤ተቻችለን መኖር እንችላለን።ቀደምት ስልጣኔ ያለን ሰዎች እንዴት ይህ ይጥፋን??
የቡድኖች መብትም ሆነ የግለሰብ መብት የሚከበርባት፤ፍትህና ሰላም የሰፈነባት ሃገር እንፈልጋለን።ልዩነቶቻችንንና ዓላማችንን በመገዳደል ሳይሆን በመወያየት እንፍታ።መወያየት የማይፈልግ ቡድን ቢኖር በፍቅር፤በአክብሮትና በማሳመን ችሎታ መለወጥ እንችላለን።ይህ አነጋገር ሞኝነት ሊመስል ይችላል፤ሆኖም ግን በማያባራ ጦርነት ወስጥ ገብቶ ከመጨራረስና የዓለም መሳቂያ ከመሆን፤የማይተካውን ክቡርና ውድ የሰው ነፍስንም ከማጥፋት የፈጀውን ጊዜ ፈጅቶ፤ዋጋ ከፍሎ በሰላምና በፍቅር መጨረስ ይሻላል።ሂትለርና ናፖሌዎን በመሳሪያ ሃይል ያልቻሉትን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በማሳየት የዓለምን ህዝብ አንድ ሶስተኛ በቢሊዮን የሚቆጠር ተከታይ አፍርቷል።ክርስቲያን ያልሆኑ ታላላቅ የዓለም ሃይማኖቶች እንኳን ክርስቶስን  ያከብራሉ፤ትምህርቱን ያደንቃሉ።በቀይ ሽብር፤በ፴ ዓመቱ የኤርትራ ነጻ አውጪ ጦርነት፤በኢትዮ ኤርትራ ያለቀውን ስናስብ ከመተላለቅ ሌላ የተሻለ መፍትሄ መፈለግ እንዳለብን ይታወቅናል።የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነውና አሁን የምናየው የመናቅ፤የመሳደብና “እኔ ብቻ ነኝ ትክክል” የሚለው መንፈስ በመከባበርና ከሌሎችም ትምህርት ማግኘት እችላለሁ በሚል የመማማር መንፈስ ካልተቀየረ ወደ አስከፊ ደረጃ በቀላሉና በፍጥነት ሊሸጋገር ይችላል።ተቃራኒ አስተሳሰብ ያላቸው ወገኖች ሁሉም ለኢትዮጵያ ጥቅም እስከሆነ ድረስ በውይይትና በመደራደር ችግሮቻቸውን ሊፈቱ ይገባል እንጂ በ ፪፩ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን ከሚያህል ታላቅ ሀገር መጠላላትና መጠፋፋት አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ የልጆቻችንን ተስፋ መግደልና በዕጣ ፈንታቸው ላይ መፍረድ ማለት ነው።አምላክ ከዚህ ይጠብቀን።
አሜሪካኖች በኢራቅና በአፍጋኒስታን የሞተባቸውን በማሰብ ፻ሺ በሶሪያ ተጨፍጭፎ እንኳን እያመነቱ ነው።ቅዱሱ መጽሃፍ “ውሻ ወደ ትፋቱ እንደሚመለስ ስንፍናውን የሚደግም ሰው እንዲሁ ነው”ይለናል።ከዚህ ፈጣሪ ይጠብቀን።
ለሃይማኖት መሪዎች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፤ከዓለምና ከአፍሪካም ቀደምት እንደመሆኗ ከሁሉም ቤተ እምነቶች አብዛኛውን ህዝብ ስለምታገለግል ለሰላም፥ለፍትህና ለዕርቅ ታላቅ ሚና መጫወት ትችላለች። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከየትኛውም ሀገር ይልቅ በሰላም አብሮ በመኖር የሚደነቁና የሚመሰገኑ ናቸው።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንዶች በስማቸውና በየዋህነታቸው በመጠቀም  አክራሪ ዓላማችውን መፈጸም ይፈልጋሉ።ስለሆነም ይህ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንዳያጋጫቸው እነዚህን ቡድኖች ከመካከላቸው ለይተው በማውጣት የተለመደውን  ሰላማዊነታቸውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።መብታቸውንም ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠየቅ መብታቸው ነው።
ካቶሊኮችና ወንጌላውያን አማኞችም በሀገራችው ጉዳይ ዳር ከመያዝ ይልቅ ቃሉ “የዓለም ብርሀን የምድር ጨው ሁኑ” ስለሚል ሰላም፤ፍትህና ልማት እንዲስፋፋ ድርሻቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።
ዋናው ብርሃን የምንሆነው በመስበክና ለእግዚአብሔር የምስጋናና የጸሎት መስዋእት ማቅረብ ብቻ ሳይሆን  በመልካም ስራችን ነው፥”መልካሙን ሰራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ”።
“የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል?… መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ  ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ።
በኛ ቤተ ዕምነት ብቻ ሳይሆን “በሰው ሁሉ ፊት”፥ይህም ማለት በሀገሪቱ በጠቅላላ ማለት ነው።ማስታረቅ፤ለፍትህና ለመልካም አስተዳደር መስራት።
ድሃን መመገብና መንከባከብ በጎ ቢሆንም ከድህነት እንዲወጣና ትክክለኛ ፍርድ እንዲያገኝ ማድረግ ዋናው ነገር ነው።
ዓሣን ከመስጠት ይልቅ ዓሣ እንዴት እንደሚጠመድ ማሳየት፤ ያ ነው ፍትህ።
ለኢትዮጵያ መንግስት
ለሰራችሁት በጎ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ይባርካችሁ።በጥሩ ስራችሁ ቀጥሉ።ፍጹም መንግስት በዓለም ላይ የለምና ብዙ የሚስተካክሉ ነገሮች እንዳሉ እናንተም የምታውቁት ነው።በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለ የተወሰነ ክፍል የሚጠይቀው የመብት ጥያቄ አለ።
እርግጥ ነው ከመብት ጋራ ግዴታዎችም አሉ።ሀገሬ ለእኔ ምን አደረገችልኝ ብቻ ሳይሆን እኔስ ለሀገሬ ምን አደረኩ የሚለውን መጠየቅ አስፈላጊ ነው።የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ የሀገሪቱን ህግ በማክበር መደረግ ሲኖርበት መለወጥ የሚገባው ህግ እንኳን ቢሆን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ማድረጉ ስልጡን ያደርገናል።
አንዳንዶች መብታችን አልተከበረም በማለት ያመረሩ አሉ።ጫካም የገቡ አሉ።መንግስት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደመቆሙ ሆደ ሰፊ በመሆን ችግሮች የሚፈቱበት፥ የተጣሱ መብቶችም የሚከበሩበትን መንገድ ማፈላለግ አለበት።
ተቃዋሚዎች ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል “የሰብአዊ መብት ጥሰት፤የመልካም አስተዳደር እጦትና ሙስና የሃገሪቷን ዕድገት ሊገቱ ይችላሉና ባስቸኳይ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፤ እነዚህን የፈጸሙ ከኃላፊነታቸው መነሳትና ለፍርድ መቅረብ አለባችው፤ፍርድ ቤቶች ራሳቸው ነጻና ገለልተኛ መሆን አለባቸው፤ህግ አውጪው፤ተርጓሚውና አስፈጻሚው በአንድ አካል ትዕዛዝ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ፍትህ ይጓደላል።የመወዳደሪያው ሜዳም ለሁሉም እኩል መሆን አለበት”የሚል ነው ።
ነገ በእግዚአብሔርም በታሪክም ስለሚያስጠይቃችሁ፤ ለልጆቻችሁም በኩራት የምትጠቅሱትን መልካም ስራ ሰርታችሁ እለፉ።”ሁሉም ያልፋል፤የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል”አሜን።
ለተቃዋሚዎች
የተቃዋሚ መኖር ለአንድ ሀገር በረከት ነው።እርግጥ ነው ፈጣሪ ዓለምን ሲገዛ ተቃዋሚ አያስፈልግም፤እርሱ ፍጹም ነውና።
ዊንስተን ቸርችል “እስካሁን ካየናቸው ስርዓቶች በስተቀር እንደ ዲሞክራሲ መጥፎ ነገር የለም” ብለዋል።”ካሉት ይሻላል፤ምርጫዬ ግን አይደለም” ለማለት ፈልገው ነው።በዲሞክራሲ ስርዓት ጠንካራ ተቃዋሚና ሚዲያ መንግስትን ለመቆጣጠር ወሳኝ ናቸው።እነሱ ከሌሉ የአገዛዙ ድክመቶች ሳይታዩ ሊያልፉ ይችላሉ።ይህ ማለት መንግስት ራሱ ከሚያካሂደው ግምገማ ተጨማሪ ማለት ነው።ተቃዋሚዎች አንድ ሆኖ መታገል ይጠበቅባቸዋል።አንድ ኣይነት ሳይሆን የሚያስፈልገው አንድነት ነው። UNIVERSITY የሚለው ቃል UNITY IN DIVERSITY  ከሚለው የመጣ ነው።በልዩነት አንድነት።ወደዚህ ደረጃ መሸጋገር ያስፈልጋል።የሚከፈለውን ሀጋዊና ሰላማዊ ዋጋ፤መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆን።
ነገ ከመንግስት ጋር መደራደር ወይንም ስልጣን መጋራት ቢመጣ አብሮ መስራት ሰለሚኖር፤በወሳኝ የሀገር ጉዳዮችም ላይ አብሮ መምከር ስለሚኖር ከአሁኑ ለዚያ የሚመጥን ስነ ምግባርና ጨዋነትን መላበስ።ላለመስማማት መስማማት።
በኢትዮጵያዉያን መካከልና በፖለቲካ መሪዎች መካከል የመረረና የማይቀለበስ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታ አለመኖሩን ለማሳየት አንዳንዴ ከገዢው ፓርቲ ጋር የሚያስማሙ ጉዳዮችን በማንሳት አብሮ መስራት እንደሚቻል ማመላከት።  በአፈታሪክ እንደተጻፈው  ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የሞተ ውሻ ባገኙ ጊዜ ሁሉም ሲጸየፉና ሲሸሹ ጌታ “አቤት ጥርሱ እንዴት ነጭ ነው” ብሎ አደነቀው ይባላል።  ምንም ጥሩ ነገር የለውም ተብሎ ከሚታመንበት ነገር ውስጥ እንደምንም ፈልጎ አንድ ጥሩ ነገር ማግኘት። ይህ ደግሞ መንግስትም ተቃዋሚዎች የሰሩትን በጎ ስራ ማበረታታትንም ያካትታል።እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች መቀራረብ፤መደማመጥም ያመጣል።ወቀሳና ክስ ብቻ ከሆነ ግን ተያይዞ ገደል መግባት ነው።
ነገ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲ ሆኖ ሊገኝ ይችላል።የዛሬ ተቃዋሚዎች ሥልጣን ከያዙ “ከተቃዋሚ ምንድነው የምጠብቀው?” ብለው ያን የሚጠብቁትን እነርሱ ዛሬ ማድረግ።”ሰው ሊያደርግላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉለት”ይላል ወርቃማው ትዕዛዝ።
ለሚዲያው
አንዳንዶች በትክክል እንደሚሉት ሚዲያው ልክ እንደ ህግ አውጪው፤ተርጓሚውና አስፈጻሚው ለሀገሪቱ ህጎች መከበርና ለፍትህ መንገስ አራተኛውን ወሳኝ ሚና ይጫወታል።ዋናው ስራ ችግሮችን እየገለጡ መፍትሔ እንዲገኝላቸው ማድረግና አንዳንድ በጎ የሆኑና ህዝቡን ለሰላምና ለእድገት የሚያነሳሱ ስራዎችን መዘገብ ነው።ከዚህ በተጨማሪ በሳይንስ፤በዕውቀት፤በመዝናኛና ሌሎችም ገንቢ ስራዎችን ያከናውናል።ሚዲያ በመሰረቱ ነጻ መሆን አለበት።እርግጥ ነው ወደ አንድ ወገን አስተሳሰብ ሊያደላ ይችላል።ይህ ግን ሙያው የሚጠይቀውን ስነ ምግባርና ኤቲክስ ሳያጓድል መሆን አለበት።ዓላማው ሀገር እንድትገነባ፤ህዝብ ከነ ልዩነቱ አንድነቱን እንዲጠብቅ፤ጥላቻና መከፋፈል እንዲወገድ   ፍቅርና ሰላምን ማበረታታት ይጠበቅበታል። በርግጥ ጋዜጠኛ የሰው ቀልብ የሚስቡና ገበያ የሚያመጡ የሚያስደነግጡ ወሬዎችን ለማቅረብ መፈተኑ አይቀርም።ያም ቢሆን እንኳን ኤቲክሱን የለቀቀና ህዝብን ከህዝብ የሚያባላ መሆን የለበትም።
የመንግስት ሚዲያዎች የአንድ ፓርቲ ልሳን ሳይሆኑ በህዝብ የቀረጥ ገንዘብ የሚተዳደሩ ስለሆነ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ሁሉንም ፓርቲዎችና ዜናዎቻቸውን በእኩልነት ደረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።የባለስልጣኖችንም የስራ ሂደት በመከታተል በጎ የሰራውንም ምሳሌ  እንዲሆን፤ፍትህ ያጓደለውም ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ተከታትሎ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል።
ዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ በተመለከተ
የዓለም መንግስታትና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች በሀገራችን ላይ ታላቅ ሚና ይጫወታሉ።በግሎባላይዜሽን ዘመን ልንሸሸው የማንችለው ዕውነታ ነው።ይህ ሕብረተሰብ  አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሚና መጫወት ይችላል።
ከአዎንታዊው ብንጀምር የገንዘብና የቴክኖሎጂ ርዳታ፤ከልምዳቸው በተለይ በሰብአዊ መብት፤ ዲሞክራሲና  ሌሎች ጉዳዮች ላይ የማሰልጠን ፤ የማማከርና የማሳሰብ ድጋፎች  መስጠት ይገኙበታል።
ወደ አሉታዊው ስንመጣ ሀገራችን በውጭ ወራሪዎች ብዙ የተፈተነች፤በሃይማኖትና በሌሎች በጎ ምግባር ስም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቅኝ ለመግዛት የሞከሩ መንግስታት ትውስታ አላት።ባሁኑም ዘመን ቢሆን አብዛኛዎቹ መንግስታት የራሳቸውን ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ በማየት እንጂ ሁሉም ለኛ አስበው እንደማይደግፉን ማወቅ ብልህነት ነው።በቅርቡ እንኳን በግብጽና በሶሪያ በመቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ እርስ በርሱ ሲተላለቅ ከሃዘን መግለጫ ውጭ ዞር ብለው አላዩትም።ይህ ለኛ ትልቅ ትምህርት ነው።እኛው ለኛ እንወቅበት።ካለኛ ለኛ ሌላ የለምና፤ከኢትዮጵያ አምላክ በስተቀር።እርሱ አንድ ያድርገን፤አሜን።አሁንም አንዳንዶች ከመካከለኛው ምስራቅ አክራሪ የእስልምና ሃይማኖትን በማስገባት በሰላም የኖረውን ህዝብ “ከርስቲያን ከሃዲ ነው፤ተለዩዋችው” በማለት አንዳንዶቹም ከዛ አልፈው” ሃይማኖቱን የቀየረ ይገደል” በማለት በሙስሊም በጎ ምግባርና ርዳታ ስም ይሄን መርዝ እየረጩ ይገኛሉ።”ባህላዊ እንጂ ዕውነተኛ ሙስሊሞች አይደላችሁም” በማለት መስጊዶችና ታሪካዊ ቦታዎችን ማቃጠል፤አብያተ ክርስቲያኖችን ሰበብ አየፈለጉ ማቃጠል ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።ህዝቡ ግን ነቅቶ እየጠበቃቸው ስለሆነ አይሳካላቸውም።ድህነታችን ከምዕራብም ሆነ ከምስራቅ ለሚመጡ ስውር ዓላማ ላላቸው መጠቀሚያ አይሆንም።
ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚለው “የኋላችንን እየረሳን ወደፊት እንዘርጋ”።አንድነት፤መከባበርና ተስፋን ይዘን ወደፊት እንሂድ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።
በስመ አብ፤ወወልድ፤ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤አሜን።
ወንጌላዊ ዳንኤል ጣሰው
ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ
Advertisements