ጋዜጣዊ መግለጫ፥ሰላምና ፍትህ ለኢትዮጵያ!

                                                   eth rise
                                                            ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ
                                                    ethiopiariseandshine.com
                                                   ethiopiariseandshine@gmail.com
                                                  001-301-909-3700(US), 09 04143933(A.A)
ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላት ስልጣኔዋ የታወቀ አገር ናት። የዓለምን ታዋቂ ሃይማኖቶች ከአብዛኛው የዓለም አገሮች ቀድማ በመቀበል የፍቅር፥የመቻቻልና የአብሮ መኖር  ተምሳሌት ናት። የሙስሊምና የክርስቲያኑ ተከባብሮ ብሎም ተዋዶና ተረዳድቶ መኖር ሰፊ ጥናት ተካሂዶበት ለዓለም ሁሉ ሞዴል መሆን የሚችል የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስልጡን አስተሳሰብ ምሳሌ ነው። በቅርቡ በተካሄደ ጥናት ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ቀዳሚ የሃይማኖት ሀገር የሚል የክብር ደረጃ ተሰጥቶናል። 

የአስተዳደር ታሪካችን ብዙ ውጣ ውረድ የበዛበትና በከፍታና በዝቅታ ያለፈ ሲሆን በዚህ ሁሉ ግን ኢትዮጵያዊነት ገንኖ እና ሁሉን አሰባሳቢ ሆኖ ቆይቷል።

በቅርቡም በሀገራችን በተከሰተው ውጥረት ውስጥ ህዝብን እንደገና እያሰባሰበ ያለው ይህች ጥንታዊትና  የእግዚአብሔር ስም ጎልቶ በወጣባት ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር ስር አንድ የመሆን ፍላጎት ነው።  
 በመንግስትና በህዝብ መካከል የሚታየው ግጭትና ውጥረት በአስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ አስከፊ ሁኔታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለዓለም የመቻቻል ምሳሌ የሆነችውን ሀገር የግጭትና የጥላቻ ማዕከል ከማድረጉም በላይ በህዝባችን ኤኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ ለዘመናት የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ሊያልፍ ይችላል። ከውርደትና ጥላቻ በስተቀር ለልጆቻችንም የምናወርሰው ቅርጽ አይኖረንም። የዓለምም መሳለቂያ እንሆናለን።
ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ይህ ሁኔታ እንዳይከሰትና ሀገራችን ለህዝቦችዋ ሰላምን፥ፍትህንና ልማትን የምታመጣ ለዓለም ምሳሌና ለልጆቻችንን መኩሪያ የምትሆን ሀገር እንድትሆን የሚሰራ አገልግሎት ነው።
በሀገሪቱም በየጊዜው በሚከሰቱት ግጭቶች ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ ወቅታዊ መግለጫዎችን አውጥቷል።
በተለይም ላለፉት ሶስት ዓመታት በመንግስት፥በሀገር ቤትና በውጭ ተቃዋሚዎች መካከል የሰለጠነ ውይይትና ድርድር እንዲካሄድ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በዚሁ መሰረት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በግለሰብ ደረጃ ተገናኘተው እንዲወያዩ መድረክ በማዘጋጀትና በማበረታታት የራሱን ሚና ተጫውቷል። በዚህም በጎና አበረታታች ውጤቶች ተገኝተዋል። ይህ ኦፊሴሊያዊ ያልሆነውን የግል ውይይት ወደ ኦፊሴሊያዊ የመንግስትና አሁን ባሉት ድርድሮች የማይካፈሉት ዋና ዋና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም መካከል እንዲካሄድ ጥረታችንን አጠናክረን የቀጠልን ሲሆን በቅርቡም እንደሚሳካ እምነታችን የጸና ነው። ይህም ውይይትና ድርድር በሀገር ቤት ያሉትን ብቻ ሳይሆን በውጭም ተደራጅተው የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉትን እንዲያካትት እያቀድን ነው። ለዚሁም እንዲረዳ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ፥ከዲያስፖራ አክቲቪስቶችና ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከስቴት ዲፓርትመንት ጋር ተነጋግረናል።
 ከሌሎችም የሰላምና የመግባባት ቡድኖች ጋር የመስራት ፍላጎት ያለን ሲሆን ከአንዳንዶቹም ጋር እየተነጋገርን ነው።
ሰላምና ፍትህ የተያያዙ ነገሮች ናቸው።አንዱ ያለ አንዱ አይሄድም። አንዳንዶች ሰላም ሰላም ይላሉ፥ ፍትህን ግን ችላ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ፍትህ  ፍትህ ይላሉ፥ ሰላምን ግን ችላ ይላሉ። ስለሆነም ሁለቱም እንደሚያስፈልጉ አምነን ጠንክረን እንስራ። ፈረንጆች Piece not Pieces, Justice Not Just Us! ይላሉ። ስለሆነም ሰላምን እንጂ ክፍፍልን አንሻም፤ ፍትህን እንጂ እኛ ብቻ የሚሉትን አንሻም።
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ።
ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ
ሬቨረንድ ዳንኤል ጣሰው
መስራችና ዳይሬክተር
 
ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ መቀመጫው በዋሽንግተን ዲሲ ሲሆን በኢትዮጵያ የሰላምና ፍትህ አጀንዳ ካላቸው የሃይማኖት ተቋማት፥የግጭት አፈታት ምሁራን፥ የሀገር ሽምግሌና ታዋቂ ሰዎች ጋር በመመካከር የሚሰራ ከመሆኑም በላይ ከመንግስትና ከተቃዋሚ አመራሮችም ጋር በቅርርብ ይሰራል።  ከዓለም አቀፉ ኮምዩኒቲም ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ይወያያል።
DPM Opp
Advertisements

ጠ/ሚ ሃይለማርያም መልቀቂያ አቀረቡ፥ አስቸኳይ መልዕክት ለአብያተ ክርስቲያናት ምዕመናንና መሪዎች

eth rise
 
ሀገራችን በብዙ ተግዳሮት ውስጥ እያለፈች መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ጊዜ ክርቲያኖችና መሪዎች አጥብቀው የሚጸልዩበትና እንደ አስቴር ከመጸለይም አልፎ ወደ ቤተ መንግስት በመሄድ እግዚአብሔር የሚያሳየንን መፍትሔ ለሀገር መሪዎች መንገርና መምከር፥ መገሰጽና መርዳት ይገባናል።ዮሴፍም፥ዳንኤልም፥መጥምቁ ዮሃንስም ይሄንን ነበር ሲደርጉ የነበረው። አንድ ወዳጄ የሆነ ታዋቂ የግጭት አፈታት ፕሮፈሰር እንደሚለው “We are not neutral but we are impartial” ማለትም ለሰላምና ለፍትህ አቋም አለን።ግን ወደተራ የፓርቲ ፖለቲካ ወርደን የአንዱ ቲፎዞ ሆኖ ሌላውን ማሰይጠን ከኛ አይጠበቅም።
በፍትህና በሰላም ጉዳይ ገለልተኛ አይደለንም የወንጌል አጀንዳ ነውና። ሆኖም ግን አድማና ቡድንተኝነት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን አትገባም። እርግጥ ክርስቲያኖች በግላቸው ከጥላቻና አመጽ ነጻ በሆነ መንገድ የአንድ ፓርቲ አባል መሆን ይችላሉ። ቤተ ክርስቲያን ግን የሁሉም እናት ሆና ስራዋ ሁሌም መፍትሔ ማምጣት፥ፈውስ መሆን ነው። ይህ ደግሞ በግል ህይወታችን ብቻ ወይንም ለአባላቶቻችን ብቻ ሳይሆን ወይንም ለአማኞች ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መፍትሔ መሆን ትችላለች፥ይገባታል። ጆን ስቶት እንዳለው ሀገርን መዳን እንዳለባት ነፍስ ማየቱ ግድ ይላል።
ወንጌል ስርጭት አንዱ መገለጫው ማህበራዊ ተሳትፎ ነው።በፍቅር ተግባር ያልታጀበ ወንጌል ሙሉ አይደለምና።
“እኛን የጎዳን የሚበድሉን በደል ሳይሆን የወዳጆቻችን የአብያተ ክርስቲያናት ዝምታ ነው”
ማርቲን ሉተር ኪንግ
“ጻድቃን ዝም ሲሉ ሀጥአን ይሰለጥናሉ፤ብልሆች በጸጥታ ሲቀመጡ ሰነፎች ይበዛሉ፤ብርሃን ካልበራ ጨለማ ያሸንፋል፤በቤተ ክርስቲያን ህንጻ ውስጥ መደበቅ ሀገር ያጠፋል፤በጸሎት ህብረት ብቻ መወሰን ህዝብ መረን እንዲሆን ያደርጋል፤በሀገራችን ጉዳይ ሳንሳተፍ መልካም ነገር እንዴት እንጠብቃለን? ያልተዘራ ይታጨዳል?” ዶ/ር ማይልስ መንሮ
 እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ

የግንቦት7 እና የኦነግ እስረኞች ሊፈቱ ነው

ሰሞኑን ከሚፈቱት እስረኞች መካከል ምህረት አይደረግላቸውም ተብለው የሚገመቱት፥ በፓርላማ አሸባሪ የተባሉት የግንቦት7 እና የኦነግ አባላት እንደሚኖሩበት አውቀናል። ከዚህ በተጨማሪ ይቅርታ እንዲጠይቁ አልተገደዱም። ይህ በእውነት ወደፊት ሊካሄድ ለሚችለው ብሄራዊ መግባባት ትልቅ ተስፋ ነው። ትጥቅ ያነገቡ ሁሉ የሀገራዊው ውይይትና ምክክር ብሎም ድርድር አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ ይሰጣል። ይህ ደግሞ በተለይ በሰላምና መግባባት ላይ ለምንሰራ ሁሉ ተስፋ ፈንጣቂ ነው። እግዚአብሄር ለሀገራችን ሰላምንና ፍትህን ያምጣልን።

መርዶክዮስ ፍትህ አጣ፥አስቴር ጾም ጸሎት አወጀች፥ከዚያስ ምን አደረገች?

መርዶክዮስ ፍትህ አጣ፥አስቴር ጾም ጸሎት አወጀች፥ከዚያስ ምን አደረገች?

ሀገራዊ ጥሪ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች

ብዙ ወገኖች የአስቴርን የሶስት ቀን ጾም ጸሎት ምሳሌ በማድረግ በተለያዩ አርዕስት ላይ ጾም ጸሎት ይይዛሉ። በቅርቡም ለሃገር እንደተጸለየ ተገንዝቢያለሁ። መልካም ነገር ነው።ጸሎት ሁኔታዎችን ለእኛ ይቀይራል ወይ እኛን ለሁኔታዎች ይቀይራል።አስቴር በመጸለይዋ ወደ ንጉሱ ለመግባት ድፍረት አገኘች፥ጥበብ ሆነላት፥ሞገስም ተላበሰች።ጸሎት የሁሉ ነገር መነሻ ነው። ያለጸሎት ምንም ነገር አይሆንም።
የብዙ ክርስቲያኖች ችግር የሚጀምረው ግን እዚህ ጋር ነው።ጸሎት ላይ ያቋርጣሉ፥ ወደሚቀጥለው ደረጃ ከፍ አይሉም።
አስቴር ከጸለየች በኋላ ግን በጸሎቷ ረክታ አልተቀመጠችም። ቃሉ እንደሚለው ያለ ህግ ቢሆንም ወደ ንጉሱ ገባች፥ንጉሱ ቢቆጣም፥ቢገድለኝም ብላ ሳትፈራ ለመርዶክዮስና ለህዝቧ ፍትህ ልትጠይቅ ወደ ንጉሱ ገባች። ሞገስ አገኘች፥ንጉሱ ተቀበላት። በድፍረትም አንደበትዋን ከፍታ የህዝቧን ብሶት ተናገረች። ሁለት ጊዜ ስብሰባ በቤትዋ አዘጋጅታ ንጉሱንና ሊያጠፋቸው የተነሳውን ሀማን ጋበዘች።
በዚህ ጊዜ ሌላ ነገር ተከሰተ። ንጉሱ መዝገብ ይምጣልኝ ብሎ ፍትህ አጥቶ ሊገደል የነበረውን የመርዶክዮስን ገድል የሚያወራ ታሪክ ወጣ። አያችሁ መርዶክዮስ በደህና ቀን በጎ ስራ ሰርቶ ነበር። በንጉሱ ላይ ሊሰራ የነበረውን ግፍ አጋልጦ ነበርና ያ ተቆጠረለት።በሞት ፈንታ እንዲከብር ተደረገ። አስቴር በግብዣዋ ላይ ሞት ያወጀባቸውን የሀማን ግፍ ለንጉሱ ተናግራ ፍትህ አስገኘች። በአስቴር ሪፖርትና በወቅቱ ሀማ ከድንጋጤ የተነሳ የማይሆን ነገር አድርጎ ነበርና ንጉሱ ተቆጥቶ በሞት እንዲቀጣ አስደርጎ አስቴርና የአይሁድ ህዝብ በግፍ ከመገደል ተረፉ፥ፍትህ አገኙ።
ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን? ከጸሎት በኋላ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል።አስቴር ጸልያ ብትቀመጥ ምንም አይሆንም ነበር። መርዶክዮስም በደህና ጊዜ በጎ ስራ ባይሰራ ኖሮ ፍትህ አያገኝም ነበር።
እባካችሁ ክርስቲያኖች፥ ጸልየን ቁጭ አንበል፥እንደ አስቴር እንውጣ፥ወደ ንጉሱ እንሂድ፥ለህዝባችን ፍትህ እንጩህ፥ብጠፋም ልጥፋ ብላ ነው የሄደችውና አትፍሩ፥ጌታ ሞገስ ይሆናችኋል።
በኢትዮጵያ ያላችሁ ክርስቲያን ወገኖቼ፥ወደ ከተማችሁ መሪዎች ሂዱ፥ስለ ፍትህ
ተሟገቱ፥አትፍሩ፥እውነትን በፍቅር ተናገሩ። እንደ ዳንኤል ለናቡከደነጾር ምክርን ምከሩ፥እንደ ዮሴፍ ለፈርኦን ጥበብን አውጁ፥ በዓለም ካለው በእናንተ ውስጥ ያለው ይበልጣልና። በአገልግሎታችን ብዙ ጊዜ ወደ መሪዎች እየገባን ስለሰላምና ፍትህ እንናገራለን፥ወደፊትም እንቀጥላለን።
ጌታ በባለስልጣኖች ፊት እንደ አስቴር ሞገስ ይስጣችሁ።መርዶክዮስም ፍትህ ያገኛል፥ከመሞትም ይተርፋል። ሞት በሃገራችን ይብቃ፥ አለአግባብ እስራት ይብቃ፥ኢፍትሃዊነት ይብቃ፥የሰብአዊ መብት ረገጣ ይብቃ፥የሰላምና የፍትህ አምላክ በኢትዮጵያ በክብር ይገለጥ፤አሜን።
ዳንኤል ጣሰው
ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ አገልግሎት
ethiopiariseandshine.com

 

ከኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ

 የኢትዮጵያ ጉዳይ አሳሳቢ ነው።ቀውሱ አልቆመም፤የመዳን ቀን ዛሬ ነው! 

በጥምቀት በዓልና በማግስቱ በወልዲያ የተፈጸመው አሳዛኝ ድርጊት ነው። ታዳጊ ወጣቶች፥ እናቶች፥በርካታ ወጣቶችና ጥቂት የጸጥታ ሃይላትም የተገደሉ ሲሆን በዘር ላይ ባነጣጠረ ጥቃት የብዙ ሰዎች ንብረትም ወድሟል።
የጸጥታ ሃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ መውሰድ የለባቸውም። መሳሪያ ላልያዙ ወጣቶች ጥይት መተኮስ ሳይሆን በሌሎች መንገዶች ጸጥታን ማስከበር ይቻላል። በወልዲያ ተመጣጣኝ ሃይል ያልተጠቀሙ ሁሉ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ። በተለይ ይህ ግድያ የተፈጸመው በተከበረ የሃይማኖት በዓል ላይ መሆኑ አሰቃቂ ያደርገዋል።
እስከዛሬ የተኬደበት መንገድ አልሰራም። መግለጫዎች፥ውይይቶችና ቃል ኪዳኖች ተግባራዊ ስላልሆኑ ችግሩ ከመቀረፍ ይልቅ የመባባስ አዝማሚያ እያሳየ ነው። አንዳንድ የብሄራዊ መግባባት እርምጃዎች መወሰድ የተጀመሩ ቢሆንም ትንሽና እየዘገዩ ስለሆነ ብዙ አልጠቀሙም። መንግስት ለብሄራዊ መግባባት ሲባል በፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸውን እስረኞችን በሙሉ በአስቸኳይ በመፍታት ዋና ዋናዎችን በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉትን ተቃዋሚዎች ስብስቦ ብሄራዊ ውይይት ዛሬ ነገ ሳይባል መጀመር አለበት፤ነጻ ሚዲያና ነጻ ምርጫ ቦርድ፥ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ባሉበት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በአስቸኳይ ይካሄድ ።
አገልግሎታችን ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ከመንግስት፥በሃገርና በውጭ ካሉ ዋና ዋና ተቃዋሚዎች፥ከአሜሪካና አውሮፓ ህብረት ጋር እንዲሁም ከሃይማኖት መሪዎችና ሌሎች የሰላም መልዕክተኞች ጋር እየተነጋገርን ከዚህ በፊት የጀመርነውን የድርሻችንን ለመወጣት እየሞከርን ነው።
የወልዲያ ወጣቶች ለባለስልጣናት ያሉት መንግስት ለጥያቄዎቻችን መልስ አሁን ይስጠን ነገ አይደለም ብለዋል።
የመዳን ቀን አሁን ነው።
በወልዲያ ቤተሰብ ለሞቱባቸው እግዚአብሔር መጽናናቱን ይስጥ እንላለን።
eth rise

ፕሬዚደንት ትረምፕ፥አፍሪካና ወዳጄ ሳም

 

ሬቨረንድ ሳሙኤል ሮድሪጌዝ የአሴምብሊስ ኦፍ ጋድ ፓስተርና የ16 ሚሊዮን ላቲኖ ክርስቲያኖች ህብረት ፕሬዚደንት ነው።ለእኔም ወዳጄ ነው። በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ አብረን ተካፍለናል።ፕሬዚደንት ትረምፕ ስልጣን የያዘ ቀን ስነ ስርዓቱን በፀሎት እንዲመራም መርጦት ነበር።የሳም መርህ ወንጌል ስርጭትን እንደ ቢሊ ግራሃም፥ ፍትህን እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ ይዘን መሄድ አለብን የሚል ነው። አሁንም ድረስ የትረምፕ አማካሪ ፓስተር ነው። ሰሞኑን ፕሬዚደንቱ በአፍሪካ ጉዳይ ተናገረ በተባለው ላይ የሚከተለውን ብሏል፥
“ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠረው፤ያለ ምንም ልዩነት። ስለሆነም ኢሚግሬሽንን በተመለከተ ሁሉም ሰው ህጉን ተከትሎ መብቱ እንዲጠበቅ ያስፈልጋል።ከናይጄሪያም ሆነ ከኖርዌይ፤ከሆላንድም ሆነ ከሄይቲ እሴታችንን እስከተቀበሉና ሸክም ሳይሆኑ ለሀገራችን ተጨማሪ ግብአት እስከሆኑ ድረስ እኩል መስተናገድ አለባቸው።ከዚህ በተጨማሪ ግን ከታላቅ አክብሮት ጋር የምናገረው ፕሬዚደንቱ አሉ የተባለው ነገር በመጨረሻው ጥሩ እይታ እንኳን ብናየው ሊባል የሚችለው የተሳሳተ፥የማይገባና ጎጂ አስተያየት መሆኑን ነው።ለምን? እግዚአብሔር እነዚህን ሀገሮች ሲያይ እንደ ልጆቹ ነውና የሚያያቸው።”

sam2

SamDan

የወንጌል አማኙ አቶ በቀለ ገርባ

ከጥቂት ጊዜ በፊት ከኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት መሪዎች አንድ ነገር ሰማሁ ስለ አቶ በቀለ ገርባ።ውይይታችን በወቅቱ የኢትዮጵያ ጉዳይና በአገልግሎታችን ኢትዮጵያ ተነሺ አብሪ ስለምናካሂደው የሰላም ጥረት ነበር። ስለ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ስንነጋገር ነው እንግዲህ የአቶ በቀለ ጉዳይ የተነሳው። አቶ በቀለ የወንጌል አማኝ እንደሆነና በግል እንደሚያውቁት አንድ የአብያተ ክርስቲያናቱ መሪ ነገሩኝ።ሲቀጥሉም በጣም የተወደደ ሰላማዊና ታማኝ አማኝ እንደሆነ በፍጹም በሌላ ነገር እንደማይሰማራ አረጋገጡልኝ። እንዲያውም ማንም ሰው ስለርሱ ማንነት መረጃ ቢፈልግ የኛ ቤተ ክርስቲያን አባል ነውና መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ አሉኝ።
በነገራችን ላይ በሌላ ጊዜ ከዶክተር መረራ ጋር ስንጫወት በኛ ፓርቲ ውስጥ እንደ በቀለ ገርባ በሰላማዊ ትግል የሚያምን የለም፤እንደውም የማርቲን ሉተር ኪንግን ነውጥ አልባ መጽሃፍ በኦሮምኛ የተረጎመ ነው ያሉኝን አስታውሳለሁ።የመጽሃፉ ስም “ህልም አለኝ” የሚል ነው።
በቅርቡ እንደተረዳሁት የአቶ በቀለ ክስ ከሽብርተኝነት ወደ ተራ የወንጀል ክስ ወርዷል። ይህን ታዋቂና ብዙ ደጋፊዎች ያሉትን ሰው እንዲሁም ሌሎች የፖለቲካ መሪዎችና ጋዜጠኞች መፍታት ለብሔራዊ መግባባት የራሱን ሚና ይጫወታል ብለን እናምናለን። በዶክተር መረራ የተጀመረው በጎ እርምጃ በዚሁ ይቀጥል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።

bekele-gerba

Bekele_Gerba1 (2)